የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት መከፈቱን ተከትሎ የቀድሞ ክለቡ ጅማ አባ ጅፋር ኦኪኪ አፎላቢን ለማስፈረም ቅድመ ስምምነት በመድረሳቸው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ይታወሳል። ሆኖም አስቀድሞ ከጅማ አባጅፋር ጋር ባደረጉት ቅድመ ስምምነት መሰረት እፈፅማለው ያለውን ክፍያ ሊያሟላ ባለመቻሉ ውሉ ሊቋረጥ እንደሚችል በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።
አሁን ጅማ አባጅፋር ክለብ አመራሮች ከኦኪኪ አፎላቢ ጋር ለመደራደር በመፈለጋቸው ተጫዋቹ ረፋድ ላይ ከአዲስ አበባ በመነሳት ጅማ ከተማ ገብቷል። ጅማ አባጅፋር ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በሚካሄደው ጨዋታ ላይ ወደ መጨረሻ ደቂቃ ላይም በስታዲየም ተገኝቷል። የሁለቱ ወገኖች ድርድር ስኬታማ የሚሆን ከሆነ ኦኪኪ የቀድሞ ክለቡን ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ የሚቀላቀል ይሆናል። በሁለተኛው ዙር አገልግሎት መስጠትም ይችላል።
ኦኪኪ አፎላቢ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር አምና የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በግሉ በ23 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ስኬታማ የውድድር ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ወደ ግብፁ ኢስማይሊ በመሄድ ያልተሳካ ቆይታ አድርጎ በስምምነት መለያየቱ ይታወቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡