የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አጃይብ አባመጫ ኦኪኪ አፎላቢ በዛሬው ዕለት የግላቸው ማድረጋቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ስኬታማ ጊዜ ካሳለፉ የውጭ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን በ23 ግቦች ካጠናቀቀ በኃላ ውስብስብ በሆኑ አወዛጋቢ ጉዳዮች ታክለውበት ወደ ግብፁ ኢስማኤል ቢያመራም እምብዛም የመጫወት ዕድል ባለማግኘቱ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡ ዳግም ከተመለሰ በኋላ የቀድሞው ክለቡን በስፋት ይቀላቀላል ቢባልም በርካታ ክለቦች እሱን ፈላጊ በመሆናቸው ወደ ጅማ የመዘዋወሩን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎት ቆይቶ ነበር፡፡
ትላንት በተስተካካይ መርሀ ግብር በሜዳው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 3-3 በተለያየበት ጨዋታ ከ84ኛው ደቂቃ በኋላ በስታዲየሙ ውስጥ የተገኘው ኦኪኪ ለክለቡ መፈረሙን ያረጋገጡት አቶ አጃይብ አባመጫ የተጫዋቹ የዝውውር ሂደት ከታክስ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ረጅም ጊዜን እንደፈጀባቸው ተናግረዋል፡፡ “እሱ ያለን ታክስ ሳይቆረጥ ንፁህ ገንዘብ ሊሰጠኝ ይገባል ነው። እኛ ደግሞ በመንግስት አሰራር መሠረት ታክስ ተቆርጦ የሚደርሰውን ገንዘብ አስቀመጥንለት ነበር። ተጫዋቹን ልንፈልግ የቻልንበት ምክንያት ደግሞ ደጋፊው ለሱ ካለው ፍላጎት አኳያ ነው። ትላንት እኔው ራሴ ትኬት ቆርጬለት ነው የመጣው። ዛሬ ደግሞ ያለውን ነገሮች ሁሉ አጠናቀናል፡፡ እሱ ባለን ነው የሄድነው፤ ምክንያቱም የደጋፊውም ጥያቄዎች ስላሉ እሱ መሄድ ባለበት ነው እኛም የሄድነው።” ብለዋል፡፡ ኦኪኪ ወርሀዊ ወደ 300 መቶ ሺህ ብር ክፍያን ክለቡ እንደሚፈፅምለትም ጭምር ተናግረዋል፡፡
የኦኪኪን መምጣት ተከትሎ የውጭ ተጫዋቾች ቁጥሩ ወደ ስድስት ከፍ ያለበት ጅማ አባጅፋር አጥቂው ቢስማርክ አፒያን ሊቀንሰው እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡