በ2010 በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ከተሾሙ በኋላ በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫው ውጤታማ የውድድር ጊዜ የነበራቸው እና በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ውድድር ውጤት የራቃቸው አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ዛሬ ከወላይታ ድቻ ጋር በስምምነት ተለያይተዋል፡፡
የክለቡ ከ17 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ዘነበ ፍሰሀ ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ ከክለቡ የለቀቁት መሳይ ተፈሪን ተክተው በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ከተሾሙ በኋላ በፕሪምየር ሊጉ ቡድኑን ለማቆየት እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ ለመታገል ቢገደዱም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ሁለት ዙሮችን መሻገራቸው እና ከአፍሪካ ታላላቅ ክለቦች አንዱ የሆነው ዛማሌክን ጥለው ማለፋቸው አድናቆት አስገኝቶላቸው ነበር። በዓመቱ መጨረሻም ቋሚ ውል በመፈረም እና በርካታ ዝውውሮች በመፈፀም የውድድር ዘመኑን ቢጀምሩም ቡድኑ በሚያስመዘግበው ደካማ ውጤት መነሻነት ከደጋፊዎች ተቃውሞ ሲሰማባቸው ቆይቷል።
አሰልጣኙ በትግራይ ስትዲየም በደደቢት ከተረቱ በኃላ ክለቡ እንዲለቃቸው ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን ከወልዋሎ በሜዳቸው 1-1 ነጥብ ከተጋሩ በኃላ ከደጋፊዎች ተቃውሞ ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከክለቡ ጋር ለመለያየት ጥያቄ ማቅረባቸውን መግለፃቸው ይታወሳል። ነገር ግን ቦርዱ ከደጋፊዎች ጋር ከተነጋገረ በኋላ በድጋሚ ሀሳባቸውን አስቀይረው ክለቡን እንዲመሩ መደረጉም ይታወሳል፡፡ ሆኖም ክለቡ በተደጋጋሚ በውጤቱ ላይ መሻሻል ባለማሳየቱ አሰልጣኙ ያቀረቡት ጥያቄ ዛሬ አመሻሽ 11:00 ላይ ተቀባይነት አግኝቶ በይፋዊ ስምምነት ከክለቡ ጋር ሊለያዩ ችለዋል፡፡
ከስንብቱ በኋላ አሰልጣኙ ለሶከር ኢትዮጵያ ይሆን ብለዋል። “በስምምነት ከክለቡ ጋር ተለያይቻለሁ። ባቀረብኩት ጥያቄ መሠረት ቦርዱ ተነጋግሮ በስምምነት ተለያይተናል። ክለቡ እና የቦርዱ አባላት በስራ በቆየሁበት ጊዜ ላደረጉልኝ አስተዋፅኦ እጅጉን አመሰግናለሁ። ጠንካራዎች ነበሩ፤ ከነሱ ጋር በመስራቴ ደስተኛ ነኝ። ከጎኔ የነበሩትም ደጋፊዎች ከልብ አመሰግናለሁ፡ ”
ከበርካታ አሰልጣኞች ጋር ስሙ እየተነሳ ያለው ወላይታ ድቻ ዋና አሰልጣኝ እስከሚሾም ድረስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚያደርገው የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በምክትል አሰልጣኙ ደለለኝ ደቻታ እየተመራ ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን ለሁለተኛው ዙር የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር እንደሚከናወን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ገና ሳይጋመስ ከአሰልጣኞቻቸው ጋር የተለያዩ ክለቦች ቁጥር ስድስት ደርሷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡