ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ

ከ15ኛው ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ቀጣዩ የቅድመ ዳሰሳችን ትከረት የደደቢት እና የሀዋሳ ጨዋታ ይሆናል።

በተስተካካይ ጨዋታ የዓመቱን 11ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ደደቢት በሜዳው ሀዋሳን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ ይጀምራል። በቅርቡ ከሽረ እንደስላሴ ጋር የተለያዩትን አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በዋና አሰልጣኝነት የሾመው ደደቢት ብሊጉ ግርጌ የመጀመሪያውን ዙር ላለመጨረስ ዕድል ከሚስጡት ሁለት ጨዋታዎች መካከል የነገው አንዱ ነው። ከደቡብ ፖሊስ ጋር ያለው የአራት ነጥብ ልዩነት እንዲሰፋ ከፈቀደ ግን የሁለተኛው ዙር ክብደት የሚጨምርበት ይሆናል። ከስምንተኛው ሳምንት በኋላ በጀመረበት ፍጥነት መቀጠል ያልቻለው ሀዋሳ በድሬዳዋ ሜዳው ላይ የተሸነፈበት ጨዋታ ወደ 4ኛነት ከፍ በማለት መሪዎቹን በነጥብ የሚቀርብበትን ዕድል አሳጥቶታል። በዕኩል ነጥብ በሚከተሉት ሦስት ክለቦች ተበልጦ በሰንጠረዡ ወገብ የሊጉን አጋማሽ ላለመጨረስም ደደቢትን አሸንፎ መመለስ ብቸኛው ተስፋው ነው።

ደደቢት አማካዩ ዓለምአንተ ካሳ እና ተከላካዩ ክዌክ ኢንዶህን በጉዳት አቤል እንዳለን ደግሞ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ የማይጠቀም ሲሆን ምንም ጉዳት እና ቅጣት በሌለበት ሀዋሳ ከተማ በከል ብሩክ በየነ ከጉዳት መልስ እንሰሚደርስ ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

–  ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው 18 አጋጣሚዎች ደደቢት 11 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 36 ግቦችን አስቆጥሯል። ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 18 ጊዜ ግብ ሲቀናው 3 ጊዜ አሸንፏል። አራት ጨዋታዎቻቸው ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 

– በአዲሱ መቀመጫው መቐለ ሰባት ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት አራት ነጥቦችን ብቻ ሲያሳካ አምስት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

– አምስት ጨዋታዎችን ከሀዋሳ ውጪ ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ ይዘው ሲመለሱ አንድም ድል አላስመዘገቡም።

ዳኛ

– እስካሁን በዳኘባቸው ሦስት ጨዋታዎች አስር የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶችን የመዘዘው ኢሳይያስ ታደሰ ሀዋሳ ከተማን አንድ ጊዜ የዳኘ ሲሆን ይህንን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነትም ተሰጥቶታል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1) 

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ዳዊት ወርቁ – ኤፍሬም ጌታቸው  – ኄኖክ መርሹ

ኩማ ደምሴ – አብርሀም ታምራት

ዳግማዊ ዓባይ –  የዓብስራ ተስፋዬ – እንዳለ ከበደ

አሌክሳንደር ዐወት

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2) 

ሶሆሆ ሜንሳህ 

 አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መሣይ ጳውሎስ

ዳንኤል ደርቤ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን –ኄኖክ ድልቢ – ያኦ ኦሊቨር

ታፈሰ ሰለሞን 

እስራኤል እሸቱ  – አዳነ ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *