ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ከ23 ወራት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

በ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ መቐለ ያመራው ሀዋሳ ከተማ በደስታ ዮሐንስ ብቸኛ ጎል ደደቢትን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

በአዲሱ አሰልጣኛቸው ዳንኤል ፀሃየ እየተመሩ ወደ ሜዳ የገቡት ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት መከላከያን ከገጠመው ቡድናቸው ኩዌኩ አንዶህን በኤፍሬም ጌታቸው፣ ዓለምእንተ ካሳን በአብርሃም ታምራት፣ ሄኖክ መርሹን በዳንኤል ጌድዮን ቀይረው ሲገቡ ሀዋሳዎች በበኩላቸው ዳንኤል ደርቤን በአክሊሉ ተፈራ፣ ሶሆሆ ሜንሳህን በተ/ማርያም ሻንቆ እንዲሁም እስራኤል እሸቱን በአስጨናቂ ሉቃስ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ካስ ተቆጣጥረው ለመጫወት በሞከሩበት የመጀመርያው 45 በእንጻራዊነት ሀዋሳዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በተለይ በሁለቱም በመስመር በኩል ዒላማቸውን አጥቂ ስፍራ ላይ የተሰለፈውን አዳነ ግርማ ባደረጉና ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች እድሎችን መፍጠር ችለዋል። ታፈሰ ሰለሞን ከርቀት ሞክሯቸው በግቡ አናት የወጡ ኳሶች እንዲሁም ከመስመር ተሻምተው በግብ ጠባቂው ረሺድ ማትውሲ እና ተከላካዮቹ የተመለሱ ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ደደቢቶችም ተጋጣሚያቸው ኳስ ከኋላ ለመመስረት በሚሞክሩበት ግዜ በፈጠሩት ስህተት በመጠቀም አሌክሳንደር ዓወት የሞከረው እንዲሁም ከግራ መስመር ዳግማዊ ዓባይ አሻምቶት አክዌር ቻሞ የሳተው የሚጠቀሱ ሙከራዎቻቸው ነበሩ።

በሀዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የቀጠለው ጨዋታው በ30ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሐንስ በግምት ከ30 ሜትር በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ ደደቢት መረብ ላይ አርፎ እንግዶቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድን በኩል ንጹህ የግብ እድል ሳይፈጥሩ እረፍት ወጥተዋል።

የደደቢቶች ብልጫ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሰማያዊዮቹ ብዙ የግብ እድሎችን ቢፈጥሩም ኳሱን ከመረብ ጋር ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይ በመድሀኔ ብርሃኔ እና አብዱላዚዝ ዳውድ ከርቀት የተደረጉ ሙከራዎች የግቡ ብረት ሲመልስባቸው አሌክሳንደር ዓወት በመቀስ ምት መትቶት ተ/ማርያም ሻንቆ የመለሰበት ከብዙዎቹ ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በመጀመርያው 45 ያገቡትን ግብ ማስጠበቅን ምርጫቸውን ያደረጉት በአዲሴ ካሳ የሚመሩት ሃዋሳ ከተማዎች አልፎ አልፎ በአስጨናቂ ሉቃስ እና አዳነ ግርማ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ረሺድ ማታውኪልን የፈተኑ አልነበሩም። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በእንግዳው ቡድን ሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ መጋቢት 20 ቀን 2009 በአዲስ አበባ ስታድየም መከላከያን 3-0 ካሸነፈ በኋላ በ26 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ድል ሳያስመዘግብ ቆይቶ በመጨረሻም ዛሬ ድል ቀንቶታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *