የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አስረኛ ሳምንት 5 የምድብ ለ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነዋል። ወልቂጤ እና መድን ተከታታይ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ አዲስ አበባ ከተማም አሸንፏል።
ቅዳሜ ድሬዳዋ ላይ በ4:00 በዓትት ድሬዳዋ ፖሊስን የገጠመው ኢትዮጽያ መድን 4-2 አሸንፈሰ ተመልሷል። ሳቢያን ሜዳ ላይ በተደረገው ጨዋታ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት መድኖች በ10ኛው ደቂቃ በአጥቂው ምስጋናው ወልደስላሴ ነበር። ድሬዳዋ ፖሊስ በ26ኛው ደቂቃ በዘርዓይ ገብረስላሴ ግብ አቻ መሆን የቻለ ቢሆንም የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ሒደር ሙስጣፋ አስቆጠረሮ በመድን መሪነት ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ ድሬዳዋ ፖሊሶች አቤል ብርሀኑ በ54ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ አቻ መሆን ቢችሉም ከ8 ደቂቃዎች በኋላ አብዱልለጢፍ ሙራድ መድንን ወደ መሪነት መልሷል። በ64ኛው ደቂቃ ደግሞ ተከላካዩ ማታይ ሉል አራተኛውን አክሎ ጨዋታው በመድን 4-2 አሸናፊነት ተደምድሟል።
በተመሳሳይ ሳቢያን ሜዳ ላይ በ10:00 ሰዓት መርሃ ግብር የወጣለት የናሽናል ሲሚንት ከ አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ በሁለቱ ቡድኖች ስምምነት አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ የተካሄደ ሲሆን እንግዳው ቡድን አአ ከተማ 3-0 ማሸነፍ ችሏል። ሳዲቅ ሴቾ በ4ኛው፣ ሙሀጅር መኪ በ52ኛው እንዲሁም በ64ኛው ደቂቃ ምንያምር ጴጥሮስ የአዲስ አበባን ጎሎች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
ዲላ ላይ በ9:00 ዲላ ከተማ ከየካ ያደረጉት ጨዋታ ያለጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የምድቡ ጨዋታዋች ዛሬም ላይ ቀጥለው መሪው ወልቂጤ ከተማ በሜዳው 3-0 ነገሌ አርሲን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል። የወልቂጤን የማሸነፍያ ጎሎች ያስቆጠሩት በ32ኛው ደቂቃ ብስራት ገበየሁ፣ በ64ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ ናቸው።
መድን ሜዳ ላይ ወላይታን ሶዶ ያስተናገደው ኢኮስኮ 1-1 ተለያይቷል። በ20ኛው ደቂቃ ዳግም ማቲዎስ ባስቆጠረው ግብ ባለሜዳውን መምራት ሶዶዎች ቀዳሚ ሲሆኑ በ58ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት የኋላሸት ሰለሞን የኢኮስኮን የአቻነት ጎል አስቆጥሯል።
በምድቡ ተጠባቂ የነበረው የሀምበሪቾ እና የሀላባ ከተማ ጨዋታ ሳይካሄድ ቀርቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡