ከፍተኛ ሊግ ሐ | ሀዲያ ሆሳዕና መሪነቱን አጠናክሯል

10ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው አቻ ውጤቶች የበረከቱበት ሳምንት ሆኖ ሲያልፍ ሀዲያ ሆሳዕና ከተከታዩ ያለውን ልዩነት በማስፋት ግስጋሴውን ቀጥሏል።

ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ተከታዩ አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። አሁን ለአርባምንጭ እየተጫወቱ የሚገኙት የቀድሞ የሆሳዕና ተጫዋቾች ለሆኑት በረከት ወልደዮሐንስ እና መስቀሉ ሌቴቦ ስጦታ በማበርከት የኢትዮጽያ ብሔራዊ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ በተጀመረው ጨዋታ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ እና በጉሽሚያዎች ምክንያት በተደጋጋሚ የሚቆራረጥ ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ሙከራ ያደረጉት ሆሳዕናዎች የአርባምንጭን ተከላካይ ክፍል በቀላሉ ሰብሮ መግባት ተስኖቸው ቢታይም ቀስ በቀስ ጠንከር ያሉ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በ17ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ኤሪክ ሙራንዳ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ለትማ ስትመለስ ተከላካዩ ትግዕስቱ አበራ በነፃ አቋቋም ሆኖ ቢያገኘውም የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። በ21ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር እዮብ በቀታ ላይ በተሰራ ጥፋት የዳኛውን ውሳኔ ተከትሎ የአርባምንጭ ተጫዋቹች በመቃወም ዳኛውን ሲከቡ ቀድሞም በመልካም ምግባራቸው የሚታወቁት አሰልጣኝ መሳይ ሜዳ ድረስ በመግባት ተጫዋቾቻቸውን ለማረጋጋት ሞክረዋል።

ኳስ ይዘው ለመጫወት የሞከሩት አርባምንጮች ወደ ተጋጣሚያቸው ሶስተኛ ክፍል ለመድረስ የሚደርጉት እንቅስቃሴዋች በተከላካዮች ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጥ ወደ መጀመሪያ አጫወታቸው የተመለሱ ሲሆን በ 31ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በስንታየው መንግስቱ አማካኝነት ማድረግ ችለዋል። በተደጋጋሚ በተጫዋቹች አላስፈላጊ ንክኪ ሲቆራረጥ የነበረው ጨዋታ ላይ የአርባምንጭ ቡድን አመራሮች እግርኳስ ከሚፈቅደው እንቅስቃሴ ውጭ በማድረግ ለአራተኛው ዳኛ የቤት ስራ ሆነውበት የዋሉ ሲሆን በተደጋጋሚ የዳኛውን ውሳኔ ሲቃወሙም ተስተውሏል። 42ኛው ደቂቃ ፍቃዱ መኮንን በሆሳዕና ተከላካይ ስህተት የተገኘችውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ብታገናኛውም ግብ ጠባቂው ቀድሞ በመውጣት ሲያድንበት የእንግዳውን ቡድን የተከላካይ መስመር አልፎ ለመግባት የተቸገሩት ሆሳዕናዎች ተጨማሪ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዋች ተጭነው የተጫወቱት ሆሳዕናዋች ሁለት አስቆጪ የግብ ሙከራዋች አድርገዋል። በ49ኛው ደቂቃ ራዛቅ አብደላ ከግራ መስመር በመነሳት የአርባምንጭን ግብጠባቂን በማለፍ ወደግብነት ለወጠው ሲባል የአርባምንጭ ተከላካይ ደርሶ ያስጣለው እና በ54ኛው ደቂቃ በድጋሚ ራዛቅ አብደላ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡ አናት ጨርፋ የወጣችበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። በ62 ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረበው እዮኤል ሳሙኤል ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት ራዛቅ ሲያሻማ ኳስ ዮሴፍ ድንገቱ ወደግብነት ለውጦት ሆሳዕናን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ውጤቱን ለማስጠበቅ ሆሳዕናዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተጋጣሚያቸው የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥረትም አድርገው ነበር። በተለይም በስንታየው መንግስቱ፣ አንድነት አዳነ እና አለልኝ አዘነ ያደረጉት የግብ ሙከራዋች ተጠቃሽ ነበሩ። በ87ኛው ደቂቃ ኤሪክ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት የወጣችበት ደግሞ በሆሳዕና በኩል ትጠቀሳለች። ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ውጤቱን ተከትሎም ሆሳዕና ምድቡን በ23 ነጥብ መምራቱን ቀጥሏል።

ሌሎች ጨዋታዎች

ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከ ቤንጅ ማጂ ቡና ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። ጨዋታው በተጀመረ በ36ኛው ሰከንድ ወንድማገኝ ኪራ የዓመቱን ፈጣን ጎል በማስቆጠር ቤነረች ማጂን ቀዳሚ ሲያደረረግ በ14ኛው ደቂቃ ሁሴን ኒጊሶ ባስቆጠራት ግብ ሻሸመኔዎች አቻ ሆነዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ሻሸመኔዎች በ64ኛው ደቂቃ አሸናፊ ባልቻ በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል ወደ መሪነት ቢሸጋገሩም በ82ኛው ደቂቃ ከማል አቶም ቤንጅ ማጂ ቡናን አቻ አድርጎ ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።

ቦንጋ ላይ ቡታጅራን ያስተናገደው ካፋ ቡና 2-0 ሲመራ ቆይቶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በ13 ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ታረቀኝ ከፋ ቡናን መሪ ሲያደርግ በ43ኛው ደቂቃ አዳነ መሪነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ሆኖም በ75ኛው ደቂቃ አየለ ፍቃዱ እንዲሁም በጭማሪ ደቂቃ ጀማል በደኬ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ቡታጅራ ከሜዳው ውጪ ነጥብ ተጋርቶ አንዲወጣ አስችሎታል።

ነቀምት ላይ ነቀምት ከተማ በ55ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ዳንኤል ዳዊት ጎል ጅማ አባ ቡናን 1-0 አሸንፏል። ዳንኤል ለተከታታይ አራተኛ ጨዋታ ጎል ማስቆጠርም ችሏል።

ቢሾፍቱ ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከሺንሺቾ 1-1 ሲለያዩ ቦረና ላይ ነገሌ ቦረና ከስልጤ ወራቤ ያለ ጎል ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *