ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ /ዩ ከ ሲዳማ ቡና

በዛሬው የወልዋሎ እና ሲዳማ ጨዋታ ዙሪያ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አዘጋጅተናቸዋል።

በሊጉ መሪነት ላይ ለውጥ ሊያመጡ ከሚችሉ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የወልዋሎ እና ሲዳማ ጨዋታ ዛሬ ረፋድ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ይደረጋል። ቡድኖቹ ካላቸው አቀራረብ ፣ ከድል መልስ እንደመገናኘታቸው እና በተለይም ከሜዳ ውጪ የሚጫወተው ሲዳማ አጥብቆ የሚፈልገው ውጤት እንደመሆኑ ብርቱ ፉክክር የሚስተናገድበት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

በ14ኛው ሳምንት ስሑል ሽረን በሜዳው በመርታት የተሳካለት የመጀመሪያው ቡድን መሆን የቻሉት ወልዋሎዎች የውድድር አጋማሹን የመጨረሻ ጨዋታቸውን ሲሆን የሚያደርጉት ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድልም አላቸው። ከዚህ ባለፈ ለመልቀቂያ ደብዳቤያቸው የተሰጠው ምላሽ እስካሁን በይፋ ያልታወቀው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ቢጫ ለባሾቹን የመጨረሻ ጥምረት ልንመለከት የምንችልበትም ጨዋታ ሊሆን ይችላል። 

ጨዋታው የዛሬውን ጨምሮ ሁለት ጨዋታዎች ለሚቀሩት ሲዳማ ቡና የትናንቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ተከትሎ በሊጉ አናት ለመቀመጥ የሚያስችለው ወሳኝ ጨዋታ ነው። በተስተካካይ መርሐ ግብር ድቻን በመርታት አራተኛ ተከታታይ ድል ያሳኩት ሲዳማዎች ወልዋሎን ካሸነፉ መሪነቱን መረከብ ብቻ ሳይሆን ከቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ጋር ያላቸውን የግብ ልዩነትም የማስተካከል አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል። በአራቱ ጨዋታዎች አስር ግቦችን በማስቆጠር ያሳኳቸው ድሎችም ከሀዋሳ ውጪ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የመጀመሪያ ጊዜ በድል ለመመለስ የሚያስችል በራስ መተማመን ሊያላብሳቸው ይችላል።

የወልዋሎ ዓ/ዩዎቹ አማካዮች ዋለልኝ ገብሬ በጉዳት አፈወርቅ ኃይሉ ደግሞ በቅጣት በዛሬው ጨዋታ የማይሰለፉ ሲሆን  የመስመር አጥቂው ኤፍሬም አሻሞ ግን  ከጉዳት ተመልሷል። ሆኖም የሬችሞንድ አዶንጎ መሰለፍ አጠራጣሪ ሆኗል። በሲዳማ ቡና በኩል ግን በወላይታ ድቻው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው ይየፊት አጥቂው መሀመድ ናስር በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ግን ዝግጁ ነው። በመሆኑም በመስመር አጥቂነት ስንመለከተው የሰነበተው ሀብታሙ ገዛኸኝ የመሀመድን ቦታ ሊሸፍን እንደሚችል ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ወደ ሊጉ በመጣበት የ2010 የውድድር ዓመት ከተገናኙባቸው ጨዋታዎች ውስጥ የመጀመሪያው 0-0 ሲጠናቀቅ ሁለተኛውን ሲዳማ በሜዳው  2-1 አሸንፏል።

– በትግራይ ስታድየም ሰባት ጨዋታዎች ያደረገው ወልዋሎ ሦስቱን በተመሳሳይ የ1-0  ውጤቶች ሲያሸንፍ ሁለት የአቻ እና ሁለት የሽንፈት ውጣቶች ገጥመውታል። 

– ሲዳማ ቡና ከሀዋሳ ውጪ አራት ጨዋታዎች ብቻ ሲሆን ያደረገው አንድ ድል ፣ አንድ ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል። 

ዳኛ

– እስካሁን በተካሄዱ ጨዋታዎች ሁለቱንም ቡድኖች አንድ አንድ ጊዜ የዳኘው ተካልኝ ለማ ይህን ጨዋታ የሚመራው ሲሆን በአራት ጨዋታዎች 17 የቢጫ እና 1 የቀይ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

ብርሀኑ አሻሞ – አስራት መገርሳ – አማኑኤል ጎበና

                                                    
ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ በቀለ – ሚሊዮን ሰለሞን

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ዳዊት ተፈራ 

ጫላ ተሺታ – ሀብታሙ ገዛኸኝ  –  አዲስ ግደይ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *