“በዚህ ሞራል ከቀጠልን ገና ጥሩ ነገር ይመጣል” አላዛር መለሰ – ደቡብ ፖሊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ በአስገራሚ ሁኔታ ጅማ አባ ጅፋርን 6-1 ካሸነፈ በኋላ የደቡብ ፖሊሱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ አላዛር መለሰ አስተያታቸውን ሲሰጡ በጅማ አባጅፋር በኩል ረዳት አሰልጣኙ ዩሱፍ ዓሊ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው የአንደኛው ዙር መዝጊያ ስለሆነ በወኔ ነው ተጫዋቾቹ የተጫወቱት። ለዛም ነው ይሄንን ውጤት ልናመጣ የቻልነው። ፍላጎታቸውም በጣም እየጨመረ እና ተጋጣሚያችንም ዛሬ ስለቀለላቸው ብዙ ጎል አግብተናል፡፡ ፍላጎታቸው እንጂ የተለየ ሚስጥር የለውም። በፊትም ውጤት ሊጠፋ የቻለው በይበልጥ ስለሚጨነቁ ነበር፡፡ አሁን ግን ያን የመጨነቅ ነገራቸውን ትተው ጭንቅላታቸውን እንዲያድሱ እና እንዲረጋጉ እየነገርናቸው በመምጣታችን ነው የተሻለ ነገርን መስራት የቻልነው፡፡

ለዛሬው ውጤት የተለየ ተጠቃሽ ምክንያት

“ብዙ ልዩነት የለውም። በፊት የነበረው አሰልጣኝ የሰራውን ነው እየሰራው ያለሁት። በፊት ለአሰልጣኝ ዘላለም ጥሩ ነገር እናሳያለን ብለው ይጨነቁ ነበር። ከዛ ነገር ወጥተው ነፃነት ሲያገኙ የመጣ እንጂ ምንም የተለየ ነገር የለውም። አንድም የፈጠርኩት አዲስ ነገር የለም። በሁለተኛው ዙር ደግሞ የተሻሉ ይሆናሉ። በይበልጥ በደረጃ ሰንጠረዡ ፉክክር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህ ሞራል ከቀጠልን ገና ጥሩ ነገር ይመጣል።

የጅማ አባጅፋሩ ረዳት አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ ከጨዋታው በኋላ ለአስተያየት ብንጠይቅም የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ዳምጠው አስተያየት እንዳይሰጡ በማድረጋቸው ማካተት አልቻልንም፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *