ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ከመመራት ተነስቶ ሰባተኛ ተከታታይ ድሉን አጣጥሟል

በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ድሬዳዋ ከተማ መቐለን አስተናግዶ በራምኬል ሎክ አማካይነት መሪ መሆን ቢችልም ከዕረፍት መልስ መቐለዎች በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና መሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ግቦች ማሸነፍ ችለዋል።

ባስላለፍነው ሳምንት አጋማሽ በ4ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ጅማ ላይ ነጥብ የተጋራው ድሬዳዋ ከተማ ፍቃድ ላይ የሚገኘው ሚኪያስ ግርማን በኃይሌ እሸቱ በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ በተመሳሳይ የ3ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ አድርጎ ፋሲልን የረታው መቐለ ከተማም ሥዩም ተስፋዬን በቢያድግልኝ ኤልያስ በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሽኩቻ የበዛበት እና በየደቂቃው የሚቆራረጥ እንቅስቃሴ የበዛበት ነበር። 14ኛው ደቂቃ ላይ ባለሜዳዎቹ በራምኬል ሎክ አማካይነት የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ኳሱን በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ በነበሩበት ሰዓት ሀብታሙ ወልዴ ጎል አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ በሚል የተሻረበት ሲሆን ከአምስት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ግን ራምኬል ሎክ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ድሬዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። የ21ኛው ደቂቃ የራምኬል ጎል የተቆጠረ ሀብታሙ ወልዴ ከመስመር ባሻገረው እና ኃይሌ እሸቱ በግንባሩ በጨረፈው ኳስ መነሻነት ነበር። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ወደ ኋላ አፈግፍገው መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት ባለሜዳዎቹ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲሰሩም ይታይ ነበር። የተቃራኒ ቡድንን ወደኋላ ማፈግፈግ የተመለከቱት መቐለዎች በፈጠሩት ጫና 28ኛው ደቂቃ ላይ በቢያድግልኝ ኤልያስ አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ ተጠቃሽ ሲሆን የአቻነቷን ግብ ማግኘት ሳይችሉ በ 1-0 ውጤት ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅተው የገቡት መቐለዎች ወደ ግብ በመድረስም የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል ያደረገው ሙከራ ወደ ድሬ ሳጥን መድረስ የጀመሩ ሲሆን ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ አማኑኤል ኦሰይ ማወሊ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ በቀጥታ በቮሊ በመምታት ግሩም ጎል አስቆጥሮ መቐለን አቻ ማድረግ ችሏል። ባለሜዳዎቹ በተጋጣሚያቸው በኳስ ቁጥጥሩም ብልጫ ተወስዶባቸው መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ ሦስት ደቂቃዎች በተጨመሩበት ቅፅበት ትተቀይሮ የገባው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ አማኑኤል በግንባር ካሳለፈለት ኳስ የድሬ መሀል ተከላካዮች አንተነህ ተስፋዬ እና በረከት ሳሙኤል አለመግባባትን ተጠቅሞ ከሳምሶን ጋር በመገናኘት ወሳኝ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አድርጓል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ስምኦን አባይ በፌደራል ዳኛ ሐብታሙ መንግስቴ ላይ ያሳዩት ያልተገባ ባህሪም የዕለቱ አነጋጋሪ ክስተት ነበር።

ውጤቱን ተከትሎም መቐለ 70 እንደርታ በ29 ነጥቦች ወደ መሪነቱ ሲመጣ በተመሳሳይ ሀለት ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ14 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *