የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-2 መቐለ 70 እንደርታ

ድሬዳዋ ላይ የተደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በእንግዳው ቡድን የ 2-1 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ጨዋታውን የተመለከቱ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።

” በራሳችን መንገድ መጫወት ነበረብን ፤ የጭንቀት ጨዋታ ምንም አይጠቅምም ” ገብረመድኅን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

” በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ስለተቆጠረብን የመረበሽ ሁኔታ ታይቶብን ነበር። ከዕረፍት መልስ ግን የራሳችን አጨዋወት ላይ ትከረት አድርገን በመረጋጋት መጫወት እንዳለብን እና ሽንፈትም ቢኖር መቀበል እንዳለብን ወሰንን ገባን። በራሳችን መንገድ መጫወት ነበረብን ፤ የጭንቀት ጨዋታ ምንም አይጠቅምም። ከዛ መንፈስ ወጥተን ተጫውተናል በተለይም በመጨረሻ ደቂቃ ተቀይሮ የገባው መሉጌታ ቁልፍ የሆነ ስራ ሰርቷል ፤ አሸንፈንም ወጥተናል። በአጠቃላይ ጥሩ ጨዋታ ነበር ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክርም ተደርጎበታል። እኛም ወደ መሪነቱ የሚያሽጋግረን ስለሆነ አስፈላጊያችን ነበር ለድሬዳዋም አስፈላጊ ነው። በጥቅሉ የሚያስደስት ጨዋታ ነበር። ”

ስለ ቀጣይ ጉዞው

” በቀጣይ በሜዳችን ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች አሉን። በነሱ ላይ ብቻ ነው ትኩረት ማድረግ የምንፈልገው። እስካሁንም እንዲህ እያልን ነው የመጣነው። የቡድኑ የማሸነፍ አዕምሯዊ ጥንካሬ ጥሩ ነው ስለዚህም ወደ ፊት ይራመዳል ብዬ ነው የማስሆነው። ”

” ጎል ከማግባት ውጪ ምንም እንቅስቃሴ አልነበረንም” ስምዖን አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

” በአጠቃላይ ሳየው ጨዋታው እስካሁን ከነበሩት ሁሉ የወረደ ነው። ይሄ ነው ብዬ የምገልፀው አይደለም። እነሱ በተደራጀ ሁኔታ ሲከላከሉ በተደራጀ ሁኔታ ሲያጠቁ ነበር። እኛ ግን ምንም የያዝነው ነገር አልነበረም። ጎል ከማግባት ውጪ ምንም እንቅስቃሴ አልነበረንም። ሰበብ ማድረግ ባይቻልም ተጫዋቼች ላይ ድካም ነበር። ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ከእስካሁኑ የወረደ ጨዋታ ነው ያደረግነው። ”

የቡድኑ መዳከም ምክንያቶች

” አንደኛ ነገር በጉዳት እና በሌሎች ምክንያቶች የሌሉ ተጫዋቾች አሉ። በተለይ መሀል ላይ የሚኪያስ አለመኖር ከፍተኛ ክፍተት እንደፈጠረ ማየት ችለናል። ካለን ስብስብ አኳያ ስናየው ደግሞ ቅያሪዎችን አድርገን በሁለተኛ ዕቅዳችን ለመጫወት ያደረግነው ጥረትም አልተሳካልንም። በቅያሪም ከነሱ ጋር ሲነፃፀር የኛ በጣም ደካማ ነው። ብልጫ ተውስዶብናል ፤ የሚያሳምንም ነው ጎሌች ሲገቡ የተሰሩ ስህተቶች እንዳሉ ሆነው። ”

ውጤት ያለማስጠበቅ ችግር

” የትኩረት ማጣት ዋጋ እያስከፈለን ነው። ነገር ግን ከሌሎች ቀናት የዛሬው የሚለየው መጨረሻ ሰዓት ላይ ይግባብን እንጂ በእንቅስቃሴ ከመጀመሪያውም ተበልጠን ነበር። ሄኔም አንዱንም ነጥብ ማስጠበቅ ትልቅ ነገር ነበር። እነዚህን ስህተቶች አርመን ለመግባት እንሞክራለን የዓለም ፍፃሜ አይደለም። ”

ከዳኛው ጋር ስለተፈጠረው ጉዳይ

” በርግጥ በጊዜው ስሜታዊ ሆኛለው። ነገር ግን ምክንያትም ነበረኝ። በዚህ ዓይነት ከባድ ጨዋታ ላይ እንዲህ ዓይነት ዳኛ መዳኘት የለበትም። በምንም መልኩ ዳኝነቱን ለሽንፈታችን ምክንያት አላደርግም። ግን ዳኛው ከ20 እና 30 ሜትር ርቀት ላይ ነበር ውሳኔዎችን ሲወስን የነበረው ፤ የአካል ብቃቱ ጥሩ አልነበረም ማለት ነው። ነገር ግን አስረግጬ መናገር የምፈልገው በዳኛው አላመካኝም ምክንያቱም ቡድኔ ጥሩ አልነበረም። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *