” በጋራ ሆነን አፍሪካን አይዞሽ ልንላት እና ልንገነባት ይገባል” ዲዲዬ ድሮግባ

አይቮሪኮስታዊው የቀድሞ የቼልሲ እና የዝሆኖቹ ኮከብ ዲዲዬ ድሮግባ በአፍሪካ የቢዝነስ እና ጤና ፎረም ጋባዥነት በአዲስ አበባ ሀያት ሆቴል በመገኘት አፍሪካ ውስጥ በማህበራዊ እና ጤና ዘርፎች እየሰራ የሚገኘውን ስራ አብራርቷል።

ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ በቅድሚያ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ጋር የተወያየው ድሮግባ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የገጠመው አቀባበል ፍፁም ያልጠበቀው እንደሆነ ተናግሯል። ” እዚህ ስመጣ የመጀመርያዬ ነው። ነገር ግን እጅግ ብዙ አፍቃሪ እንዳለኝ ተረድቻለሁ። ” ብሏል።

ድሮግባ ጨምሮም ” አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አሁን ላይ የመደመጥ እና የመታየት እድል አላት። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተበታተንን ልጆቿ አቅማችንን አጎልብተን፣ ተምረን፣ ሰልጥነን እና ሰርተን ተመልሰናል። አሁን በጋራ ሆነን አፍሪካን ተባብረን አይዞሽ ልንላት እና ልንገነባት ይገባል። በጋራ ከሆንን የማንችለው ነገር የለም። ” ሲል በጋራ የመስራት አስፈላጊነትን ገልጿል።

ከእግርኳስ ራሱን ካገለለ በኋላ ራሱ ባቋቋመው ፋውንዴሽን አማካኝነት በትምህርት እና ጤና ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሆነ የተናገረው ዲዲዬ በሀገሩ ትምህርት ቤት ከፍቶ ሙሉ ለሙሉ ዲጂታል የትምህርት አሰጣጥ እንዲሆን ከማስቻሉ በተጨማሪ የእናቶች እና ህፃናት ጤና ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጿል። ወደፊትም በትምህርት እና ጤና ላይ ይበልጥ አተኩሮ መስራት እንደሚፈልግ የገለፀው ድሮግባ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚቻለው እንደ አንድ ሆኖ በትብብር በመስራት እንደሆነ ተናግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *