አዳማ ከተማ ከሦስት ተጫዋቾቹ ጋር በስምምነት ተለያየ

በክረምቱ የዝውውር ወቅት በከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ጥሩ የውድድር ጊዜ አሳልፈው ለአዳማ ከተማ ከፈረሙት መካከል ከሦስቱ ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ሲለያዩ አንድ ተጫዋች በፍጥነት ከቡድኑ ጋር እንዲቀላቀል ትዕዛዝ ተላልፎበታል።

ከጅማ አባቡና ጋር አምና በከፍተኛ ሊግ የተሳካ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ አዳማ ከተማን መቀላቀል የቻለው አማካዩ ሱራፌል ጌታቸው ከቡድኑ ጋር ከተለያዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆናል። ተጫዋቹ በፕሪምየር ሊጉ አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ተቀይሮ በመግባት የተጫወተ ሲሆን ከ6ኛው ሳምንት ጀምሮ ከ18 ተጫዋቾች ዝርዝር ውጪ ሆኖ ቀይቷል።

ከሰበታ ከተማ በክረምቱ ዝውውር አዳማ ከነማን በመቀላቀል በአዲስ አበባ ሲቲካፕ ካልሆነ በቀር በፕሪምየር ሊጉ ላይ በአንድም ጨዋታ መሳተፍ ያልቻለው አማካዩ አዲስዓለም ደሳለኝ ሌላው ከአዳማ ጋር የተለያየ ተጫዋች ነው። አዲስዓለም በሦስት ጨዋታዎች ላይ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጠ ሲሆን እንደ ሱራፌል ሁሉ ከስድስተኛው ሳምንት ጀምሮ ከ18 ተጫዋቾች ዝርዝር ውጪ ሆኖ ቆይቷል።

ሌላው በአዳማ ከተማ ተስፋ ቡድን አድጎ የነበረውና አምና ከከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሰበታ ከተማ ወደ አዳማ ማምራት የቻለው የግራ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ ካሳሁን በየትኛውም የአዳማ ጨዋታ ላይ ተሳትፎ ሳያደርግ በስምምነት መለያየቱ ታውቋል።

በሌላ ዜና የ2010 የውድድር ዘመን ጅማ አባቡና እየተጫወተ በከፍተኛ ሊግ 20 ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ብዙዓየሁ እንደሻው ዘንድሮ አዳማ ከነማን በመቀላቀል የተሳካ የውድድር ጊዜ ያሳልፋል ተብሎ ቢጠበቅም በሁለት ጨዋታዎች ተቀይሮ በመግባት መጫወት ከመቻሉ ውጭ ብዙም የመሰለፍ ዕድል ባለማግኘቱ የተነሳ ደስተኛ ባለመሆኑ ከ21 ቀናት በፊት ያለ ክለቡ ፍቃድ ተነስቶ ወደ ጅማ መሄዱ ታውቋል። ሆኖም የክለቡ አሰልጣኞች በእርሱ ላይ እምነት ያላቸው በመሆኑ በፍጥነት ቡድኑን ተቀላቅሎ ልምምድ እንዲጀምር እና ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ክለቡ የዲሲፕሊን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ሰምተናል።

ለሁለተኛው ዙር ራሱን በተሻለ ሁኔታ አጠናክሮ ለመቅረብ ብሩክ ቀልቦሬን በማስፈረም ወደ ዝውውሩ የገባው አዳማ ከተማ በቀጣይ ቀናት ውስጥ አዳዲስ ፈራሚዎች ወደ ቡድኑ ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *