ስሑል ሽረ አዲስ ዋና አሰልጣኝ ሾመ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ስሑል ሽረ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥሯል፡፡

ስሑል ሽረ በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ እየተመራ የሊጉ ሊጉ ተሳታፊ ቢሆንም በወራጅ ቀጠና መገኘቱ፤ በተለይም በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለማሸነፍ መቸገሩ አሰልጣኙ ዳንኤል ፀሐዬ፣ ረዳቱ እና ቡድን መሪው ከክለቡ እንዲሰናበቱ ከተደረገ በኃላ በቴክኒክ ዳሬክተርነት ሲሰሩ የነበሩት ገብረኪሮስ አማረን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ያለፉትን ጥቂት ጨዋታዎች ሲመራ ቆይቶ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን ለመቅጠር ከውሳኔ ላይ ደርሰል። አሰልጣኝ ሳምሶን ከቡድኑ ጋር በቃል ደረጃ ከተስማሙ ቀናትን ያስቆጠሩ ሲሆን ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ከቡድኑ ጋር አብረው ተጉዘውም ነበር። ዛሬ ምሽትም በይፋ የቡድኑ አሰልጣኝ የሚያደርጋቸውን ኮንትራት ተፈራርመዋል።

አመዛኝ የተጫዋችነት ዘመናቸውን በእርሻ ሰብል ያሳለፉት ሳምሶን በሐረር ቢራ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ረዳት በመሆን ወደ አሰልጣኝነት ህይወት የገቡ ሲሆን በሐረር ቢራ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ዳሽን ቢራ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል። ለጥቂት ጊዜያት ያለ ስራ የቆዩት ሳምሶን በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ስሑል ሽረን የመታደግ ከፍተኛ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

በተያያዘ…

ስሑል ሽረ ዛሬም ከአንድ ተጫዋች ጋር ተለያይቷል። የተከላካይ አማካዩ አሸናፊ እንዳለ ምሽቱን ከቡድኑ ጋር በስምምነት መለያየቱ የተረጋገጠ ሲሆን ከሄኖክ ብርሀኑ፣ ሄኖክ ካሳሁን እና ኪዳኔ አሰፋ በመቀጠል ከቡድኑ የለቀቀ አራተኛው ተጫዋች ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *