የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ግማሽ ዓመት ስብሰባ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዝዮን የመጀመርያ የውድድር ዘመን አጋማሽ ሪፖርት እና ውይይት ሐሙስ ከረፋድ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል።

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የሴቶች እግርኳስ ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሶፊያ አልማሙን በተገኙበት በተከናወነው ስብሰባው የውድድሮቹ አጠቃላይ ሪፖርት በውድድር ከፍተኛ ባለሙያው ከበደ ወርቁ የቀረበ ሲሆን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲሁም ቁጥራዊ መረጃዎች ቀርበዋል።

በመቀጠል ስለ ሁለተኛው ዙር መርሐ ግብር እና የጥሎ ማለፍ ውድድር ዕጣ አወጣጥ በጌታቸው የማነብርሀን የተብራራ ሲሆን ውድድሮች በሚያዝያ ወር እንዲጠናቀቅ መታቀዱን በመግለፅ በተለያዩ እርከኖች የሚገኙት ሴት ብሔራዊ ቡድኖች ለሚጠብቃቸው ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በቂ የመዘጋጃ ጊዜ እንዲያገኙ ለማስቻል በጊዜ ማጠናቀቅ እንዳስፈለገ ገልፀዋል።

ከሻይ እረፍት በኋላ በቀጠለው ስብሰባ ከክለብ ተወካዮች በርካታ ሀሳቦች ተነስተዋል። ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ነቸው፡-

አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው (ንግድ ባንክ)

” ከዚህ ቀደም ይቆራረጥ ነበር። ዘንድሮ ይሀሰ ተቀርፏል። ነገር ግን ውድድሮቹ ከተጠናቀቁ በኋላ እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ ያለው ክፍተት ሰፊ ነው። ይህ ቢታሰብበት መልካም ነው።

” ክልሎች ጥሩ ስራ እየሰሩ ነው። ለምሳሌ ዲላ ላይ ለሴቶች ያለው ትኩረት ከወንዶቹ ያልተናነሰ ነው። ስታድየም የሚገባውም በክፍያ ነው። ይህ በሌሎች ቦታዎችም የሚለመድበት መንገድ ቢመቻች ”

አሰልጣኝ መሠረት ማኒ (አአ ከተማ)

” ከሊጎቹ በተጨማሪ በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ደረጃ ውድድር መኖሩን ሰምተናል። ጥሩ ጅምር ነው። ነገር ግን ከዚህ በላይ መስራት አይቻልም ወይ? ግራስ ሩት ላይ ለመስራትስ ምን ታስቧል?

” በሪፖርቱ ላይ ውድድሩ በቂ የሚዲያ ሽፋን እንዳገኘ ተገለረጿል። ነገር ግን ጥቂት ጋዜጠኞች ናቸው የሚመጡት።

” በፈረሱ ቡድኖች ላይ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ምን ጥረት አደረጋችሁ? ፈርሰዋል የሚል ሪፖርት ብቻ በቂ አይደለም። ለቀሩት ቡድኖችስ ዋስትናችን ምንድነው?

” ውድድሩን ይበልጥ ለማሳመር ፕሮግራም አወጣጥ ወሳኝነት አለው። ተደራራቢ ከሆነ ጥራቱ ይወርዳል። የተጫዋቾች አካል ብቃት፣ ዝግጅት፣ የጉዞ ሁኔታ እና የመሳሰሉት ነገሮች ታሳቢ መደረግ አለባቸው።

” ብሔራዊ ቡድኑንም፣ ውድድሩንም አብሮ ማስኬድ የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ሊጉ ቶለ የሚጠናቀቅ ከሆነ ለብሔራዊ ቡድን የማይመረጡ ተጫዋቸችን እያባከንን ነው።

” የሴቶች ልማት ኮሚቴ ውስጥ የተካተቱ ግለሰቦች ማንነት ቢታወቅ። ከአቶ ብርሀኑ ውጪ እነማን እንደሆኑ እና ስለሚሰሩት ስራ ቢብራራ

” በዳኝነቱ ላይ የተሻለ ውድረር ጊዜ አሳልፈናል። ሆኖም ተመሳሳይ ዳኛ አንድ ቡድንን በተደጋጋሚ የማጫወት ነገር ይታያል። ”

ደረጄ ታመነ (ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ)

” ስለ ጥሎ ማለፉ የተብራራበት መንገድ ግልፅ አይደለም። በተጨማሪም ክለቦችን ባላሳተፈ መልኩ ራሳችሁ ዕጣ አውጥታችሁ መላካችሁ አግባብ አይደለም። ”

አዜብ ኪዳነ (ልደታ)

” ወንድ ዳኞች በሴቶች ውድድር ላይ መመደባቸው ጥሩ ቢሆንም ለሴቶች እግርኳስ የሚሰጡት ግምት አነስተኛ ነው። ”

ሲሳይ ዳኜ (ንፋስ ስልክ)

” ኮሚኒኬ የሚላከው በኢሜይል ብቻ መሆን አማራጭ ያጠባል። በኢሜይል መጠቀም የማይቻልበት ወቅት ሲኖር ሌላ አማራጭ ያስፈልጋል። ”

መካሻው ዓለም (ፋሲል ከነማ)

” ወንድ ዳኞች እንዲዳኙ መደረጉ ጥሩ ነው። በተለያዩ ሊጎች ያላቸውን የማጫወት ልምድ ያላቸው በመሆኑ ለሴቶች ማካፈል ይችላሉ።

” አሁን 22 ቡድኖች መኖራቸው ብቻ መመልከት የለብንም። በቀላሉ የሚፈርሱ ከሆነ ቀጣይ ዓመት ወደ 15 የማይወርድበት ምክንያት የለም። ”

” የስፖርታዊ ጨዋነት ደረጃ አሰጣጥ ግልፅ አይደለም። የሜዳ ውስጥ ጉዳዮች እና የኮሚሽነር ሪፖርት ብቻ መታየት የለበትም። ”

ከክለብ ተወካዮች አስተያየት በኋላ የፌዴሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ምላሾች የተሰጡ ሲሆን በመርሐ ግብር መደራረብ ላይ ለተነሳው ቅሬታ ኢ/ር ጌታቸው ከሁለት ጨዋታ በኋላ ወደ መደበኛ መንገድ የሚመለስ መሆኑን ሲያስረዱ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን በጫና ውስጥ የማጫወት ልምድ ሊያካብቱ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በመጨረሻም የሴቶች ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሶፊያ ልማሙን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በኮሚቴው ውስጥ አብረዋቸው የሚሰሩ ግለሰቦችን አሳውቀዋል። በዚህም መሠረት ብርሀኑ ከበደ ምክትል ሰብሳቢ ሲሆኑ በለጥሽ ገብረማርያም፣ ታማር ከበደ፣ እንደገና ዓለምዋሶ እና አክበረት ተመስገን አባላት እንዲሁም አልማዝ በፀኃፊነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የአንደኛ ዲቪዝዮን ቀጣይ ጨዋታ


12ኛ ሳምንት


ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2011

መከላከያ ከ አዳማ ከተማ

ጥሩነሽ ዲባባ ከ ሀዋሳ ከተማ

ጥረት ኮርፖሬት ከ አዲስ አበባ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ድሬዳዋ ከተማ ከ ጌዴኦ ዲላ


ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2011

ኢት/ንግድ ባንክ ከ ኤሌክትሪክ

የሁለተኛ ዲቪዝዮን ቀጣይ ጨዋታ

8ኛ ሳምንት

ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011

ቂርቆስ ከ ንፋስ ስልክ

መቐለ 70 እንደርታ ከ አቃቂ ቃሊቲ

ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2011

ቦሌ ከ ፋሲል ከነማ

ልደታ ከ ሻሸመኔ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *