ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር ወደ ድል በመመለስ ደረጃውን አሻሽሏል

በ6ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ደደቢትን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡

ጅማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ፖሊስ አስደንጋጭ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ውስጥ አራት ቅያሪ በማድረግ ዘርይሁን ታደለ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና ሄኖክ ገምቴሳን በማሳረፍ ዳንኤል አጄ፣ ዐወት ገብረሚካኤል፣ ይሁን እንደሻው እና ንጋቱ ገ/ስላሴን ሲያካትት በ4-3-3 አሰላለፍ ወደሜዳ ገብቷል። በደደቢት በኩል በሜዳቸው በሀዋሳ ከተማ ከተረታው ስብስባቸው የሁለት የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ዳንኤል ጌዲዮንን በሄኖክ መርሹ፣ አክዌር ቻምን በያሬድ መሐመድ በመተካት በ 4-2-3-1 አሰላለፍ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመሩት ባለሜዳዎቹ ወደ ወደ ደደቢቶች የግብ ክልል ለመድረስና ግብ ሙከራ ለማድረግ የቻሉት በመጀመሪያው ደቂቃ ነበር። የጨዋታው ፊሽካ ተነፍቶ የተጀመረውን ኳስ በቀኝ መስመር ማማዱ ሲዲቤ ወደ ደደቢቶች ግብ ክልል ውስጥ በመግባት ወደ ግብ የሞከረውን የግቡን ቋሚ በመለተም የወጣው የመጀመርያው የጨዋታው ሙከራ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ከተሻጋሪ እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች በመጠቀም በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ደደቢቶች በይሁን እንደሻው እና አዳም ሲሶኮ ያደረጓቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ አስደንጋጭ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ከአምስተኛው ደቂቃ በኋላ የጨዋታው ፍጥነት እየቀነሰ ሲሄድ በጨዋታ እንቅስቃሴ ረገድ ደደቢቶች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም ኳስን እንደመቆጣጠራቸውና ከወሰዱት ብልጫ አንፃር ወደ ግብ በመድረስ በኩል ደካማ ነበሩ። በ11ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ኩማ ደምሴ በግምባሩ ገጭቶ ዳንኤል አጄ እንደምንም ካወጣው ሙከራ ውጭም ኢላማውን የጠበቀ ሙራ ማድረግ አልቻሉም፡፡
በመሀል ሜዳ ላይ ጅማዎች በሰው ቁጥርም ሆነ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው በመሆኑ ከመስመር ተከላካዮች በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚደርጓቸው ጥረቶች ውጤታማ አልነበረም። የመጀመሪያው አጋማሽም ከላይ ከተጠቀሱት አጋጣሚዎች በቀር ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳይታይበት ነበር የተጠናቀቀው።

ከእረፍት መልስ ጅማዎች በእለቱ ብዙ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ኳስ ሲያባክን የነበረው አምበሉ ኤልያስ አታሮን በተስፋዬ መላኩ በመቀየር ወደ ጨዋታው ሲገቡ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የመጀመርያዎቹን አስር ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብክልል ለመድረስ ሞክረዋል። በ49ኛው ደቂቃ ይሁን ከግራ መስመር ወደቀኝ ይሁን ያሻገረውን ኳስ ዲዲዬ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ረሺድ ማታውሲ በጥሩ ብቃት አድኖታል። በ53ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ተስፋዬ መላኩ በግንባሩ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ የጨዋታው ሚዛን ወደ ደደቢቶች ያደላና መሐል ሜዳ ላይ የሚንሸራሸሩት ኳሶች በርክተው ወደ ግብ የሚደርሱ እቅስቃሴዎች አነስተኛ ነበሩ። በተጨማሪም ጅማዎች በተሻለ ሁኔታ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ቢደርሱም በዕለቱ ጠንካራና በተደራጀ መልኩ ሲከላከል የነበረውን የደደቢት ተከላካይ ክፍልን አልፈው የግብ ሙከራ ማድረግ ተቸግረዋል። ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅም በሁለተኛው አጋማሽ የጅማ ደጋፊዎች በቡድኑ አመራሮች ላይ ለረጅም ደቂቃዎች ያሰሟቸው ተቋውሞዎች ትኩረትን የሳቡ ነበሩ።

በድሉ ተጠቅሞ ሶስት የአንደኛ ዙር ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ጅማ አባ ጅፋር ነጥቡን 17 አድርሶ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ደደቢት በ4 ነጥቦች ግርጌ ላይ ተቀምጦ የውድድር ዘመኑን አጋምሷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *