የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ሁለተኛ ዙር ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀመር አቃቂ ቃሊቲ ተከታዩ መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ልዩነቱን አስፍቷል። ቂርቆስ እና ንፋስ ስልክ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
በአዲስ አበባ ስታድየም 8:00 ላይ ቂርቂቆስ ክፍለ ከተማ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የቻሉት ቂርቆሶች በ2ኛው ደቂቃ በሬዱ በቀለ በግንባሯ ገጭታ ግብ ጠባቂዋ በዳነችባት ኳስ የግብ የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን አድርገዋል። በ10ኛው ደቂቃ ደግሞ ሠላም ለገሰ ከግራ መስመር አክርራ የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ጨርፋ የግቡ አግዳሚን ለትሞ ሲመለስ የንፋስ ስልክ ተከላካዮች መዘናጋት ታክሎበት አጥቂዋ ጋብርኤላ አበበ በቀላሉ አስቆጥራ ቂርቆስን ቀዳሚ አድርጋለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላ መነቃቃት ያሳዩት ቂርቆሶች በሬዳ በቀለ እና በእየሩሳሌም ብርሃኑ ተጨማሪ ሙከራ አድርገዋል። በተቃራኒው ተዳክመው የታዩት ንፋስ ስልኮች የመጀመሪያውን የግብ ሙከራቸውን ለማድረግ ግማሽ ሰዓት ጠብቀዋል። በ32ኛው ደቂቃ እየሩስ ወንድሙ ያደረገች ሲሆን ቀስ በቀስ የተወሰደባቸውን የጨዋታ ብልጫ በማስመለስ በትግስት ሹኩሪ እንዲሁም በእየሩስ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ጎል ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በቂርቆስ መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ተሽለው የገቡት ንፋስ ስልኮች በኳስ ቁጥጥር እንዲሁም ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ ነበሩ። በ66ኛው ደቂቃ ላይ በላይነሽ ልንገርህ ኳስ በአግባቡ ሳታርቅ የቀረችውን ኳስ ለማዳን የወጣችው ግብ ጠባቂዋ ዓይናለም ሽታዬ በመዓዛ መገርሣ ላይ በሰራችው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ የመሐል ዳኛው ዘግይታ ውሳኔ ማስተላለፏ በቂርቆስ በኩል ቅሬታ ተስተውሎል። የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምትም እየሩስ ወንድሙ ወደግብ በመለወጥ ንፋስ ስልክን አቻ ማድረግ ችላለች።
ንፋስ ስልኮች በጎሉ በመነቃቃት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ እየሩስ ወንድሙ እንዲሁም ትዕግስት ሹክር ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበር። በተለይም እየሩስ ወንድሙ በግራ በኩል በግሏ ስትፈጥረው የነበረው ጫናም ከፍተኛ ነበር። በቂርቆስ በኩልም በተመሳሳይ በቀኝ በኩል እየሩሳሌም ብርሃኑ ስታደርገው የነበረው ጥረት እና ሙከራ ግብ ውጤት ባይገኝበትም መልካም የሚባል ነበር።
መቐለ ላይ በሳምንትቱ ተጠባቂ ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን ያስተናገደው መቐለ 70 እንደርታ 1-0 ተሸንፏል። ለአቃቂ ቃሊቲ የሊጉን መሪነት ያጠናከረችውን ወሳኝ ጎል ያስቆጠረችው ቤዛዊት ንጉሴ ናት።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡