‹‹ የመልሱን ጨዋታ እስክንጨርስ ድረስ ጨዋታው አልተጠናቀቀም›› ክላውድ ሌርዋ

የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክላውድ ሌርዋ ከጣፋጭ የሜዳ ውጪ ድላቸው በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ በሃገራቸው የደረሰውን የሽብር ጥቃት ማዘናቸውን በመግለጽ ጋዜጣዊ መግለጫውን ጀምረዋል፡፡

‹‹ ጋዜጣዊ መግለጫውን ከመጀመራችን በፊት ትናንት በፓሪስ ያጋጠመውን አስከፊ ጥቃት ማስታወስ እፈልጋለሁ። ካፍ በጨዋታው መጀመሪያ ላይ ትናንት በዚህ ጥቃት ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ባለማዘጋጀቱ አዝኛለሁ። ›› ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ሌርዋ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እስከ መጨረሻው መታገልም እንዳስደነቃቸው ተናግረው የማጥቃት አጨዋወታቸው ለድል እዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስከጨዋታው መጨረሻ ድረስ ተስፋ ባለመቁረጥ በመጫወታቸው ላደንቃቸው እወዳለሁ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ካየሁት ጀምሮ ትልቅ አክብሮት የምሰጠው ቡድን ነው። በበርካታ ግቦች የታጀበ ጥሩ ጨዋታ አድርገናል። የእኔ የስልጠና ፍልስፍና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በሄድንበት ሁሉ ግቦችን እናስቆጥራለን። ››

አሰልጣኙ በመጨረሻም በመልሱ ጨዋታ ሳይዘናጉ በትኩረት እደሚጫወቱ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ የመልሱን ጨዋታ እስክንጨርስ ድረስ ጨዋታው አልተጠናቀቀም። የኢትዮጵያ ቡድን አምና ባማኮ ላይ የማሊ ብሔራዊ ቡድንን 3-2 ያሸነፈበት ጨዋታ ቡድኑ ከሜዳው ውጪም ማሸነፍ እንደሚችል ያሳያል። ለብራዛቪሉ ጨዋታ በቂ ዝግጅት ማድረግ እና ጨዋታውንም በጥንቃቄ ማከናወን ይገባናል። ባጠቃላይ ግን ከባድ ጨዋታ እንደሚገጥመን አውቀን ነበር፤ በውጤቱ ግን እጅግ ደስተኛ ነን።››

 

ያጋሩ