ሴቶች ጥሎ ማለፍ | እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፉ ሦስት ቡድኖች ታውቀዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ትላንት ቀጣሎ ሲካሄድ መከላከያ፣ ሃዋሳ ከነማ እና ጌዲዮ ዲላ ተጋጣሚያቸውን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።

አዲስ አበባ ስታዲየም 08:00 ላይ በተካሄደው የመከላከያ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ቡድኖቹ ካላቸው ወቅታዊ ጥሩ አቋም አንፃር ጠንካራ ጨዋታ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም እጅግ የተቀዛቀዘ እና በጎል ሙከራዎች ያልታጀበ በመሆን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ወደ ቀጣይ ዙር አላፊ ቡድን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምትም መከላከያ በግብጠባቂዋ ማርታ ምርጥ ብቃት ታግዞ 6 – 5 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ወደ አሰላ ከተማ ያቀኑት ሃዋሳ ከተማዎች ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ተመልሰዋል። አጥቂዋ ልደት ተሎዓ ሀዋሳዎችን ቀዳሚ ማድረግ ስትችል ነፃነት መና እና ስንታየሁ ማትዮስ ሌሎች ተጨማሪ ጎሎችን በማከታተል አስቆጥረው ሀዋሳ ከተማ ከሜዳቸው ውጭ ወደ ሩብ ፍፃሜ ያመሩበትን ውጤት አስመዝግበው ተመልሰዋል።

በተመሳሳይ ድሬደዋ ስታዲየም 10:00 ላይ በተካሄደው ሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በርካታ የመጀመርያ ተሰላፊዎቹን አሳርፈው ወደ ሜዳ የገቡት የድሬ እንስቶች በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠረ ጎል በጌዲዮ ዲላ ሽንፈትን አስተናግደዋል። የጌዲዮ ዲላን ብቸኛ ጎል ተቀይራ የገባችው ቤተል ጢባ ነበር ያስቆጠረችው።

የውድድሩ መርሐ ግብር

አንደኛ ዙር

ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2011

9:00 መቐለ 70 እንደርታ ከ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ

ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2011

9:00 ቂርቆስ ከ ንፋስ ስልክ

ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011

9:00 ልደታ ክ/ከ ከ ሻሸመኔ ከተማ

* ቦሌ ከፋሲል የሚያደርጉት ጨዋታ በፋሲል አለመካፈል ምክንያት ቦሌ ወደ ሁለተኛ ዙር በቀጥታ አልፏል።

ሁለተኛ ዙር

ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011

ኢት/ንግድ ባንክ 2-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

እሁድ የካቲት 10 ቀን 2011

መከላከያ 0-0 (6-5) አዳማ ከተማ
ጥሩነሽ ዲባባ 0-3 ሀዋሳ ከተማ
ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ጌዴኦ ዲላ

ወደፊት ቀናቸው የሚገለፅ

– ቂርቆስ/ንፋስ ስልክ ከ ልደታ/ሻሸመኔ
– መቐለ/አቃቂ ከ ቦሌ

* ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ከተማ ባለመሳተፋቸው ምክንያት ጥረት እና አርባምንጭ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *