የአምብሮ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስምምነት ዝርዝር

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአምብሮ የእግርኳስ ትጥቆች አምራች ኩባንያ ጋር ለቀጣይ አራት ዓመታት አብሮ ለመስራት ውል መፈፀሙን ተከትሎ ስለ ስምምነቱ ዝርዝር፣ ከጣልያኑ ኤርያ ጋር ስላለው ቀሪ ውል እና ተያያዥ ጉዳዮች የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲሱ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን ጋር ሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ከአምብሮ ጋር ለመስራት ብዙ ውጣ ውረዶች እንደነበሩ የገለፀው ባህሩ ከኤርያ ጋር የነበረው ውል የተቋረጠበትን ምክንያት እንዲህ ገልጿል። “የጣላያኑ ኤሪያ ጋር ቀሪ የሁለት ዓመታት ውል አቋርጠን ነው ወደ አምብሮ የመጣነው። ከኤርያ ትጥቅ አምራች ጋር ያለውን ነገር ግልፅ ለማድረግ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኩባንያው በዓመት 90ሺ ዩሮ ክፍያን ይፈፅማል። ከዚህም በተጨማሪ ለሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ነበር (ወንድ እና ሴት) በይፋ ትጥቁን የሚያቀርበው። ሌላውን ከነሱ መግዛት ወይም ሌላ የትጥቅ ብራንድ ለመጠቀም እንገደድ ነበር። (ለኦሊምፒክ ማጣርያ ብሔራዊ ቡድኑ አዲዳስን መጠቀሙ አይዘነጋም)። ሌላው አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ሳይመጣ በፊትም በአብዛኛው የስፖርቱ ቤተሰብ እንዲሁም በጋዜጠኞች የሚቀርቡት ትጥቆች የጥራት ጉድለት እንደነበረባቸው በይፋ ሲናገሩ ነበር። አሁን ላይ እያንዳንዱን ነገር ለማስተካከል እንፈልጋለን። ኢትዮጵያን እንደምታህል ሀገር ስናስበው በተለያዩ ውድድሮች ላይ የተለያየ የትጥቅ ብራንድ አድርጎ መግባት የለብንም። ” ብሏል።

ኃላፊው አክሎም ከኤርያ ጋር የሚፈርሰውን ውል የካሳ ክፍያ እንደሚፈፅሙ ገልጾ የካሳ ክፍያውን የመረጡት ከአምብሮ ውል ጠቀሜታ ጋር አነፃፅረው የተሻለ ሆኖ በማግኘታቸው እንደሆነ ተናግሯል። ” ከኤሪያ ጋር ባለን ስምምነት ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት የምንከፍለው የነበረው 180 ሺህ ዩሮ ነው። ነገር ግን ውሉ ሲፈርስ አፍራሹ ወገን የሚከፍለው 100 ሺ ዩሮ ነው። ውሎን አፍርሰን ወደ አዲሱ ትጥቅ አቅራቢያችን አምብሮ ለመምጣት ስንወስን የምናገኘውን እና የምናጣውን ነገር በደንብ ተወያይተንበት ነው። ከእኛ ጋር ሲስማማ ያየነው ነገር ቢኖር የሚቀርበውን ትጥቅ ብዛት ምን ያህል ነው? ጥራቱስ? ለነማን አቅርቦ ያውቃል? የሚሉትን ግምት ውስጥ አስገብተን ነበር። ኤሪያ ለሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ብቻ ሲያቀርብ በአንፃሩ አምብሮ ለስድስቱም ብሔራዊ ቡድናችን ያቀርባል። ከትጥቅ ውጭ ቱታዋች፣ የመመገቢያ ልብሶች፣ ካሶቲኒዎች፣ ቦርሳዋች እንዲሁም ወደፊት በጋዜጣዊ መግለጫ የሚጠቀሱ ቁሳቁሶችን በሙሉ በነፃ የሚያቀርብ ሲሆን በትጥቅ ዲዛይኑ ላይም ተሳትፎ አድርገናል። ” ብለዋል።

የእንግሊዙ የትጥቅ አምራች ኩባንያ ከፌዴሬሽኑ ጋር በገባው ውል መሰረት በዓመት ለሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች ከ900 በላይ ትጥቆችን ለማቅረብ ምንም ክፍያ የማይቀበል ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚኖርበት ወጪ ትጥቁ የሚመጣበትን የመጓጓዣ ወጪ መሸፍን ነው። ቀረጡን በተመለከተ ደግሞ ስፖርት ኮሚሽን የሚከፍል መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ስምምነት ዙርያ ተጨማሪ ዝርዝሮችን፣ ከውሉ በስተጀርባ የሚነሱ ጥያቄዎች እና የመሳሰሉትን በቀጣይ የምናቀርብ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *