ኢትዮጵያ ቡናን በጊዜያዊነት የሚመሩት አሰልጣኝ ታውቀዋል

በዛሬው ዕለት በይፋ ከዋና አሰልጣኙ ዲዲዬ ጎሜስ ጋር የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና ገዛኸኝ ከተማን በጊዜያዊነት ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል።

ለረጅም ዓመታት በወጣት ቡድኑ አሰልጣኝነት እና በተለያዩ አሰልጣኞች ስር የዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ሲሰሩ የቆዩት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ወደ ቡድኑ የሚመለሱት በጊዜያዊነት ሲሆን ስለ ኮንትራት ሁኔታቸው ግልፅ አልተደረገም።

አሰልጣኝ ገዛኸኝ በ2009 መጥፎ ጅማሬ ያደረጉት ሰርቢያዊው ኒቦሳ ቪሴቪችን ስንብት ተከትሎ በጊዜያዊነት በመምራት የውጤት መሻሻል ቢያሳዩም የዓመቱ መጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ከቦታው ተነስተው በዕድሉ ደረጄ መተካታቸው የሚታወስ ነው።

አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፎ የመጀመርያውን ዙር የፈፀመው ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ ገዛኸኝ ስር መጋቢት 1 ወደ ድሬዳዋ አምርቶ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታውን ከድሬዳዋ ከተማ ሲያደርግ በኢትዮጵያ ዋንጫ መጋቢት 7 ስሑል ሽረን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያስተናግዳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *