ቢኒያም በላይ ወደ ስዊድን አመራ

ከስከንደርቡ ጋር ሁለት የተሳኩ ዓመታት ያሳለፈው ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ የስዊድኑ ክለብ ሴሪያንስካን ተቀላቀለ።

በመጀመርያ ዓመት የስከንደርቡ ቆይታው ብዙም የመሰለፍ ዕድል ያላገኘው ቢንያም በሁለተኛው የውድድር ዓመት ግን ጉዳት እስኪያጋጥመው ድረስ በመደበኛነት ጨዋታዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ከአልባንያው ቻምፒዮን ጋር ባለፈው ሳምንት የተለያየ ሲሆን በአውሮፓ ሁለተኛ ክለቡ የሆነው ሴሪያንስካን ተቀላቅሏል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይ በዚቬደን ሚሎሶቪች ወደሚሰለጥኑት ሴሪያንስካዎች ማምራቱን ተከትሎ በሶስት የተለያዩ ጊዜያት ለክለቡ ከተጫወተው ዩሱፍ ሳላህ በመቀጠል ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ይሆናል።

በ2018 ከስዊድን ሦስተኛ የሊግ እርከን (ዲቪዥን አንድ) በመለያ ጨዋታ ወደ ሁለተኛው እርከን (ሱፐርታን) ያደገው ሴሪያኖስካ ከአንድ ወር በኋላ በሚጀምረው የስዊድን የሊግ ውድድር ላይ ዳገርፎርስን በሜዳው በመግጠም ከ2013 በኋላ ወደ ዋናው ሊግ የመመለስ ፈተናውን ይጀምራል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *