ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | ንግድ ባንክ ከኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርቶ መሪነቱን አስረከበ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የሁለተኛው ዙር በሳምንቱ አጋማሽ ሲጀመር አንድ ቀሪ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ተካሂዶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

በጨዋታው ጅማሬ በተደጋጋሚ የኢትዮ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በር መፈተሽ የጀመሩት ንግድ ባንኮች ገና በ3ኛው ደቂቃ በጉዳት ለወራት ከሜዳ የራቀችው ዓይናለም አሳምነው ከእርሷ በተሻለ ነፃ አቋቋም ለቆመችው ረሂማ ዘርጋው በቀላሉ መስጠት የምትችለውን ራሷ ለመጠቀም አስባ ግብጠባቂዋ እስራኤል ከተማ ባዳነችባት ሙከራ ነበር የጨዋታውን የመጀመርያ ዕድል የፈጠሩት። ብዙም ሳይቆይ ራሷ ዓይናለም አሳምነው ከሽታዬ ሲሳይ በጥሩ ሁኔታ የተሰጣትን ኳስ ተቀብላ አገባችው ሲባል ወደ ላይ የሰደደችው ሌላ ጥሩ የማግባት አጋጣሚ ነበር። ከወትሮ በተለየ ሁኔታ እንደ ቡድን መጫወት በቻሉት ኤሌክትሪኮች በኩል 7ኛው ደቂቃ ወርቅነሽ መልመላ ጥሩአንቺ መንገሻን በማለፍ ወደ ጎል የመታችው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣባት የመጀመርያ ሙከራ ነበር።


ጨዋታው ተመጣጣኝ በሆነ ፉክክር ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ቀጥሎ ከሳጥን ውጭ አክርራ አለምነሽ ገረመው የመታችው ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰው እና 22ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን የንግድ ባንክ ግብጠባቂ ንግስቲ ለማውጣት ስትል እዛው የቀረውን ኳስ ወርቅነሽ ሳትጠቀምበት የቀረችው አጋጣሚ በኢትዮ ኤትሪክ በኩል ተጠቃሽ የግብ ዕድል ነበሩ። ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ በ43ኛው ደቂቃ በንግድ ባንኮች በኩል ብዙነሽ ሲሳይ ከሳጥን ውጭ የመታችው ግብጠባቂዋን አልፎ ጎል ተቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ተከላካይዋ ሃና ታደሰ በፍጥነት ደርሳ ኳሱን ወደ ውጭ ካወጣችው የግብ ዕድል ውጭ ሌሎች ሙከራዎችን አልተመለከትንም።

ከእረፍት መልስ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ከጨዋታው አንድ ነጥበ የፈለጉ በሚመስል መልኩ ወደ ኋላ በማፈግፈግ በጥንቃቄ ሲከላከሉ የታየ ሲሆን አንድም ወደ ጎል ደርሰው የፈጠሩት የግብ አጋጣሚ አልነበረም። ኤሌክትሪኮች በአመዛኙ መከላከላቸውን ተከትሎ ጫና ሲፈጥሩ የቆዩት ንግድ ባንኮች 66ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው ላይ የተሰራውን ጥፈት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሽታዬ ሲሳይ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። በተደጋጋሚ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ቢደርሱም በተደራጀ ሁኔታ እንደ ቡድን ሲከላከሉ የነበሩትን ተከላካዮች አልፈው ጎል ለማስቆጠር ሲቸገሩ ታይቷል። ይም ቢሆን 77ኛው ደቂቃ ሽታዬ ሲሳይ ነፃ የሆነ የጎል እድል አግኝታ በግቡ አናት የሰደደችው ኳስ ንግድ ባንኮችን መሪ ማድረግ የምትችል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።


በመጨረሻም ኢትዮ ኤሌትሪኮች የፈለጉትን የአቻ ውጤት ለማሳካት ያደረጉት ጠንካራ መከላከል ተሳክቶላቸው ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ከአዳማ ከነማ ጋር በነጥብ እኩል ቢሆንም ብዙ ባገባ ተበልጦ ለወራት የያዘውን የአንደኝነት ደረጃ ሁለተኛ በመሆን ለአዳማ አንደኝነቱን ሲያስረክብ በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንድ ደረጃውን አሻሽሎ 10ኛ መሆን ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *