ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ፋሲል ከነማ

በሊጉ የመጀመርያ ዙር ከሚቀሩት ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ውስጥ ነገ አባ ጅፋር እና ፋሲልን በሚያገነኘው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

አባ ጅፋር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከሞሮኮው ሀሳኒያ አጋድ ጋር በነበረበት ጨዋታ ምክንያት የተላለፈው ይህ ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ ጅማ ላይ ይደረጋል። 14ኛ የሊግ ጨዋታውን የሚያደርገው ጅማ አባ ጅፋር በያዝነው ሳምንት አጋማሽ መከላከያን 1-0 መርታቱን ተከትሎ ወደ ሰንጠረዡ ወገብ የተጠጋ ሲሆን ከነገው ተጋጣሚው ፋሲል ቀጥሎ 6ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ የሚያችለውን ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባል። ጅማዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያሳኳቸው ድሎች ከ1-0 ውጤት ያለፉ ባይሆኑም ከደቡብ ፖሊስ ሽንፈት እና ከግብ ጠባቂያቸው ዳንኤል አጄዬ መመለስ በኋላ መረባቸውን አለማስደፈራቸው በራስ መተማመናቸውን የሚመልስላቸው ጠንካራ ጎን ነው። የአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድን በነገው ጨዋታ አምበሉ ኤልያስ አታሮን እና ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለን በጉዳት ሲያጣ ዛሬ ልምምድ ያልሰራው ዐወት ገብረሚካኤልም መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

የመጀመሪያ ዙር ጨዋታውን ነገ የሚያገባድደው ፋሲል ከነማ በድል ከተመለሰ ነጥቡን 27 በማድረስ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ይችላል። ይህ ከሆነም ውጤቱ በ22 ነጥቦች 6ኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀበት የአምናው የውድድር ዓመት በእጅጉ የተሻለ ይሆንለታል። ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች እና ከመቐለው ሽንፈት በኋላ በሱራፌል ዳኛቸው ድንቅ ግቦች ታግዘው ስሑል ሽረን 3-0 በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ዐፄዎቹ ግብ ወደ ማስቆጠሩ መመለሳቸው ከተጋጣሚያቸው ወቅታዊ የመከላከል አቋም መስተካከል ጋር መገናኘታቸው ትኩረት የሚስብ ነው። በርግጥ ቡድኑ ወደ ኋላ በሚያፈገፍግባቸው ወቅቶች በአጫጭር ቅብብሎች ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ፍጥነት ዝግ ማለት እንዲቸገር ሊያደርገው ቢችልም የሱራፌል ረጅም ኳሶች እና የሳጥን ውጪ ጠንካራ ምቶች አሁንም ልዩነት የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል። ፋሲሎች ሙጂብ ቃሲም እና ፋሲል አስማማውን ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ወደ ጅማ ይዘው መጓዛቸው መልካም ዜና ሲሆንላቸው ሰዒድ ሁሴን እና አብዱርሀማን ሙባረክ ግን በገጠማቸው ጉዳት ከቡድኑ ውጪ ሆነዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የቅርብ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ የተገናኙት አምና አባ ጅፋር ወደ ውድድሩ ሲያድግ ሲሆን ጅማ ላይ ፋሲል 1-0 አሸንፎ ሲመለስ የጎንደሩ ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– በሜዳው ያለውን ያለመሸነፍ ጉዞ 19 ያደረሰው ጅማ አባ ጅፋር ከዘንድሮዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሦስቱን ሲያሸንፍ በሦስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

– በአምናው የውድድር ዓመት ከጅማ በድል በመመለስ ብቸኛው ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ድል አስመዝግቦ ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋራ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።

ዳኛ

– በዘንድሮው የሊጉ ውድድር አምስት ጨዋታዎችን የዳኘው አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ ይመራዋል። ሁለቱን ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዳኘው አርቢትሩ በቀይ ካርድ ያሰነበተው ተጫዋች ባይኖርም እስካሁን 23 የቢጫ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጃዬ

ያሬድ ዘድነህ – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ

ይሁን እንዳሻው – ንጋቱ ገብረስላሴ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሠለሞን ሐብቴ – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ኤፍሬም ዓለሙ – ሐብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ኢዙ አዙካ – ዓለምብርሀን ይግዛው


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *