ከፍተኛ ሊግ ለ | መድን ተጠባቂውን ጨዋታ በማሸነፍ ከወልቂጤ ጋር በነጥብ ተስተካክሏል


የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ መድን በሜዳው ወልቂጤ ከተማን በማሸነፍ ነጥቡን ከተጋጣሚው ጋር አስተካከሏል። ሀላባ አስደንጋጭ ሽንፈት ሲያስተናግድ ቀሪዎቹ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ተጠባቂው የምድብ ለ ጨዋታ 09:00 መድን ሜዳ ላይ እረፍት አልባ እንቅስቃሴን አስመልክቶን በኢትዮጵያ መድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ብዛት ያላቸው የስፖርት ቤተሰቦች እና በርከት ያሉ የወልቂጤ ደጋፊዎች በተገኙበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ወልቂጤዎች በከፍተኛ ሁኔታ በተደጋጋሚ ወደ መድን የግብ ክልል ቢደርሱም ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። የወልቂጤዎች በብስራት ገበየሁ ከቆሙ ኳሶች ወደ ጎል የሚመታቸው ኳሶች ግን ለመድን ተከላካይ እና ግብጠባቂው ፈተና ነበሩ።

መድኖች አጀማመራቸው ጥሩ ባይመስልም ብዙም ሳይቆዩ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡ ሲሆን በ8ኛው ደቂቃ ምስጋናው ወ/ዮሀንስ ያቀበለውን ሚካኤል ለማ በጥሩ ሁኔታ ጎል አስቆጥሮ ቀዳሚ መሆን ቻሉ። ስህተት ሳይበዛበት በማራኪ የጨዋታ ፍሰት ቀጥሎ ወልቂጤዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ በሚያደርጉት ጥረት 22ኛው ደቂቃ ብስራት ገበየሁ ከሳጥን ውጭ የመታውን ኳስ የመድኖቹ ግብጠባቂ ጆርጄ ደስታ እንደምንም አድኖበታል።

ከመድን መሪነት አምስት ደቂቃዎች በኋላ ከማዕዘን ምት የተሻረውን ወልዳይ ገ/ሥሳሴ በመቀስ ምት ግሩም ጎል አስቆጥሮ ወልቂጤዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። ሆኖም መድኖች ወደ መሪነታቸው ለመመለስ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም፤ 32ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልለጢፍ ሙራድ ከወልቂጤ የግብ ክልል ቀኝ መስመር አንስቶ ፍጥነቱን በመጠቀም ተጫዋቾችን በማለፍ ሳጥን ውስጥ በመግባት ነፃ አቋቋም ለሚገኘው ምስጋናው ወ/ዮሀንስ ጎል አስቆጥሮ መድኖችን መሪ አድርጓቸዋል።

ከእረፍት መልስ በአመዛኙ ከመጀመርያው አጋማሽ በንፅፅር ቀዝቀዝ ብሎ በቀጠለው ጨዋታ እንግዶቹ ወልቂጤዎች በተለመደ አጨዋወታቸው ከቆመ ኳስ የግብ እድል ፈጥረዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ብስራት ያሻገረውን ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ ቢገጨውም በንቃት የግብ ክልሉን ሲጠብቅ የዋለው ግብጠባቂው ጆርጆ ደስታ በቀላሉ የያዘበት ፣ 77ኛው ደቂቃ ከወልቂጤዎች በኩል ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው እና ዓምና ከተስፋ ቡድን ጀምሮ እስከ ዋና ቡድን በኢትዮጵያ መድን መጫወት የቻለው ወጣቱ አብዱልከሪም ወርቁ በጥሩ መንገድ ለሀብታሙ ታደሰ አቀብሎት ለጥቂት የውጭ መረቡን ነክቶ የወጣው ኳስ ወልቂጤዎችን አቻ ማድረግ የሚችሉ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

የጨዋታው እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ እየያለ ቀጥሎ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተመታውን ኳስ የመድኑ ተከላካይ ማታይ ሉል በራሱ ጎል ላይ ሊያስቆጥር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ግብጠባቂው ጆርጅ ታደሰ እንደምንም አድኖታል። ቀሪዎቹን ደቂቃዎች መድኖች ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረጉት የጥንቃቄ መከላከል ረድቷቸው ከእረፍት በፊት በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።

ረፋድ 04:00 በኦሜድላ ሜዳ በተካሄደ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ከ ዲላ ከተማ 0-0 ተለያይተዋል። እንግዶቹ ዲላ ከተማዎች ላለመውረድ እንደሚጫወት ቡድን መከላከልን ምርጫቸው በማድረጋቸው በጥንቃቄ እየተከላከሉ በሚገኙት አጋጣሚዎች የሚፈጥሩት የግብ ዕድል ጠንካራ ነበሩ። ለዚህም ማሳያ 13ኛው ደቂቃ አጥቂው ኤልያስ እንድርያስ የፈጠረው የጎል አጋጣሚ ተጠቃሽ የሚሆን ነው። አዲስ አበባዎች በአንፃሩ ኳሱን ተቆጣጥረው ብልጫ በመውሰድ በተሻለ ሁኔታ ወደ ፊት በመሄድ ለማጥቃት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ቢሆንም በጎል ሙከራ ያልታጀመ በመሆኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ዘግይተዋል። 22ኛው ደቂቃ ዓለማየሁ ሙለታ አቀብሎት አስራት ሸገሬ ወደ ውጭ የወጣበት፤ ብዙም ሳይቆይ ሙሐጅር መኪ ግራ እግሩ አክርሮ የመታውን የጌዲዮ ግብጠባቂ ተካልኝ ኃይሌ እንደምንም የያዘበት መልካም የሚባሉ የግብ ዕድሎች ነበሩ ።

አአ ከተማዎች አስቀድሞ ከፈጠሯቸው የግብ የማግባት ሙከራዎች በተሻለ 29ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ሴቾ ግልፅ የሆነ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምባት ወደ ውጭ የሰደዳት ኳስ የምታስቆጭ ሆና አልፈለች። ዲላዎች በጥሩ መከላል 26ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ተሻግሮ በተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ኳስ ከሳጥን ውጭ አጠንክሮ አስቻለው ማሞ ቢመታውም ጎል መሆን ሳይችል የቀረው፤ 32ኛው ደቂቃ በዲላ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው ኢብራሂም ቢያኖ የመታውን የአዲሰ አበባ ግብጠባቂ ዋኬኔ አዱኛ ያወጣበት በዲላ በኩል የተፈጠሩ የግብዕድሎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ምንም የግብ ሙከራ ሳይደረግ ቆይቶ 62ኛው ደቂቃ የጨዋታው ዋና ዳኛ አዲሱ ሐምሳሉ እና የአዲስ አበባው ተጫዋች አስራት ሸገሬ ጋር በጨዋታው እንቅስቃሴ ሲተላለፉ ተጋጭተው ሁለቱም ሲጎዱ በተለይ የጨዋታው ዋና ዳኛ በደረሰበት የአፍንጫ መሰበር ብዙ ደም የፈሰሰው ሲሆን ህክምና እስኪያገኝ ድረስ ጨዋታው ለ25 ደቂቃ እንዲቋረጥ አስገድዷል። በዚህም ምክንያት አራተኛው ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ጨዋታውን ይመራዋል ተብሎ ቢጠበቅም ራሱ መምራት እንደሚችል በማሳወቁ የተቋረጠው ጨዋታ ሊቀጥል ችሏል።

ከዚህ ትዕይንት በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች ውጥረት እና እልህ የተቀላቀለበት ሆኖ ቀጥሎ አዲስ አበባዎችም በተሻለ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን የፊት አጥቂዎቻቸው ያገኙትን አጋጣሚ አለመጠቀማቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። 66ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ሴቾ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ኳሱን አጥብቆ ባለመምታቱ ያመከናት ፣ የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የመስመር አጥቂው እሱባለው ሙልጌታ ከኢብሳ በፍቃዱ ያቀበለውን ኳስ አገባው ተብሎ ሲጠበቅ በግቡ ቋሚ ታኮ የወጣው የግብዕድሎች የሚያስቆጩ ነበሩ። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ሰአት ለማባከን ሞክረሀል በሚል በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ኢብራሂም ቢያኖ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል። ጨዋታውም ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ ከ ኢኮስኮ ያደረጉት ጨዋታ በእንግዳው ቡድን 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሄኖክ አወቀ በ19ኛው፣ አበበ ታደሰ በ65ኛው እንዲሁም ይበልጣል ሽባባው በ89ኛው ደቂቃ ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

አርሲ ነገሌ ላይ ነገሌ አርሲ ከሀምበሪቾ 2-2 ተለያይተዋል። በግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ባለሜዳዎቹ በ25ኛው ደቂቃ ላይ የነበረ ቢሆንም በ39ኛው ደቂቃ ተስፋሁን ተሰማ ባስቆጠራት ግብ አቻ በመሆን ወደ እረፍት አምርተዋል። በ76ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ ሀምበሪቾን ወደ መሪነት ማሸጋገር ቢችልም አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አርሲዎች በፍፁምቅጣት ምት ጎል አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ የካ ክፍለ ከተማ ከድሬዳዋ ፖሊስ 1-1 አቻ ሲለያዩ ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከተማ ከ ናሽናል ሲሚንት ያለምንም ግብ ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *