ከአርሰናል ጋር በመተባበር ለፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች የሚሰጠው ስልጠና ዛሬ ተጀመረ


በሚካኤል ለገሰ እና አብርሃም ገ/ማርያም


ዳሽን ቢራ በቅርቡ ከአርሰናል እግርኳስ ክለብ ጋር የፈፀመው የቢራ ፓርትነርሺፕ ስምምነት አካል የሆነው የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ ሱሉልታ በሚገኘው ያያ ቪሌጅ ተከናውኗል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት ፓትሪክ እና ቶም የተባሉ ከአርሰናል የመጡ አሰልጣኞች ሲሆኑ ከፕሪሚየር ሊጉ 14 ክለቦች የተውጣጡ ዋና እና ረዳት አሰልጣኞችን ጨምሮ 32 አሰልጣኞች በስልጠናው ላይ ተካፍለዋል፡፡ በዛሬው እለትም የንድፈ ሀሳብ ትምህርቶች በባለሙያዎቹ ሲሰጥ ከ8፡00 ጀምሮ ደግሞ በሜዳ ላይ የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የጠዋቱ መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዳሽን ቢራ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መክብብ አለሙ ፣ የአርሰናል እና ዳሽን ፓርትነርሺፕ ክፍል ሃላፊ ኔይል ሃርቪ እና የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ቶም ኬንዲ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

 

dashen arsenal 1

‹‹ ይህ ስልጠና እስከ ታዳጊ ቡድን አሰልጣኞች ድረስ ወደፊት ይቀጥላል ›› አቶ መክብብ አለሙ

‹‹ባለፈው እንደገለፅነው ከአርሰናል እግርኳስ ክለብ ጋር የ3 አመት የአጋርነት ውል ፈጥረናል፡፡ በስምነታችን መሰረት ከያዝናቸው ፕሮግራሞች መካከል ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና አንዱ ነው፡፡ ወደፊት ከታዳጊዎች ስልጠና ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ስጠናዎችን ለማዘጋጀት አስበናል፡፡ ዛሬ ያዘጋጀነው ለፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች ስልጠና ነው፡፡

‹‹ ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት የዳሽን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክለቦች ማደግ ወሳኝ ነው ብለን እናስባለን፡፡ ለዚህም ነው ይህን ስልጠና ያመቻቸነው፡፡ ከዚህ በፊትም እንደ ልማታዊ ድርጅት በስታድየሞች ግንባታ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተናል ፤ የስፖርት ክለብም መስርተናል፡፡ በፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች የጀመርነው ከላይ ጀምረን ወደ ታች ለመቀጠል በማሰብ ነው እንጂ ወደፊት እስከ ታዳጊዎች ስልጠና ድረስ እንቀጥላለን፡፡ ››

 

‹‹ ወደፊት በመሰረተ ህዝብ እና ወጣቶች ስልጠና ላይም ማገዝ እንፈልጋለን›› ኔይል ሀርቪ

‹‹ እንደ አርሰናል እግርኳስ ክለብ ከዳሽን ጋር በጋራ ለመስራት እዚህ በመገኘቴ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በኢትዮጵያ ካሉን ደጋፊዎች ጋር የበለጠ ለመቅረብ ለኛ ጠቃሚ ነው፡፡ ወደፊት በመሰረተ ህዝብ እና ወጣቶች ስልጠና ላይም ማገዝ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ››

‹‹ይህ ስልጠና የሚጠቅመው የአሰልጣኞችን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው›› ቶም ኬንዲ

እዚህ የተገኘነው ሲኒየር የፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች እንዴት መስራት እንዳለባቸው ስልጠና ለመስጠት ነው፡፡ በተለይም አሰልጣኝ አርሴን ዌንገር ከመጡ ወዲህ በአመታት ያዳበርነው የአርሰናል ፍልስፍና ፣ ተጫዋቾችን የማብቃት ፣ የወጣት ቡድኖች ሲስተም እና የራሳችን የሆነ የአጨዋወት ስታይል አለን፡፡ የእግርኳስ ፍልስፍናዎች በየሃገሩ ያለው ተቀባይነት የተለያየ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ የምናስተምረው አሰልጣኞች ለተጫዋቾች እንዴት ማስተማር እንዳለባቸውና የተጫዋቾቹን ብቃት እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህ ስልጠና የሚጠቅመው የአሰልጣኞችን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ››

 

ዛሬ የተጀመረው ስልጠና ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ያጋሩ