የ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ የጉልበት ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ያለፉትን ስድስት ወራት ወደ ሜዳ ያልተመለሰው የቅዱስ ጊዮርጊሱ የግራ መስመሩ ተከለካይ መሐሪ መና ለተሻለ ህክምና ነገ እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ህንድ ያቀናል።
በህንድ በሚኖረው የተወሰኑ ቀናት ህክምና ጉልበቱ ላይ ቀዶ ጥገና የሚያደርግ ሲሆን ህክምናውን በተሳካ ሁኔታ አጠነቆ ሲመለስ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ቢያንስ የስምንት ሳምንት ጊዜ ሊያስፈልገው እንደሚችል ይገመታል።
ያለፉት ስድስት ወራት በእግርኳስ ህይወቱ ፈታኝ ወቅት እንደሆነ የሚናገረው መሐሪ ” በእግርኳስ ህይወቴ እንዲህ ያለህ ጉዳት አጋጥሞኝ አያቅም፤ ይህ የመጀመርያዬ ጉዳት ነው። ከልምምድ ሜዳ ርቄ የማላቅ ሰው እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥመኝ በጣም ነው የተረበሽኩት፤ የተደናገጥኩት። ” ሲል ስለ ጉዳቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል። አክሎም ” ክለቤ ላደረገልኝ ድጋፍ ከልብ አመሰግናለው። ከጉዳቴ በፍጥነት አገግሜ ክለቤን ለማገልገል በጣም ቸኩያለው።” ብሏል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጉዳቶች ያጋጠማቸውን አሉላ ግርማ፣ ሳላዲን በርጌቾ፣ ታደለ መንገሻ፣ ሳላዲን ሰዒድ እና ናትናኤል ዘለቀ ከሀገር ውጭ ህክምና እንዲያገኙ ሙሉ ወጪ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር መሸፈኑ ይታወቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡