ኤልያስ ማሞ ወደ ድሬዳዋ አምርቷል

ከቀናት በፊት ጅማ አባጅፋርን በስምምነት ለቆ የነበረው አማካዩ ኤልያስ ማሞ ማረፊያው ድሬዳዋ ከተማ ሆኗል፡፡

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ወደ ቻምፒዮኖቹ ጅማ አባ ጅፋር ያመራው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኤልያስ ማሞ በጅማ አባጅፋር የአንድ ዓመት ኮንትራትን ተፈራርሞ የነበረ ቢሆንም የአምስት ወራት ቆይታን ካደረገ በኋላ ቀሪ ኮንትራት እያለው ክለቡን ከቀናት በፊት በስምምነት መልቀቁ ይታወሳል። አማካዩ በዚህ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ድርድር ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በአንድ ዓመት ውል ወደ ምስራቁ ክለብ ማምራት ችሏል፡፡

በአዲሱ ሚሌንየም ወደ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጋር የተዋወቀው ኤልያስ ከ2003 እስከ 2006 በንግድ ባንክ ቆይታን ካደረገ በኋላ ለኢትዮጵያ ቡና እስካለፈው የውድድር ዓመት ድረስ ተጫውቷል። በተለያዩ ጊዜያት ለብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለ ሲሆን በ2007 ኢትዮጵያ ላይ ተስተናግዶ የነበረው የሴካፋ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ መመረጡም የሚታወስ ነው።

ከኤልያስ ቀደም ብሎ ምንያህል ተሾመን ያስፈረመው ድሬዳዋ ከተማ በፈጣሪ አማካይ እጥረቱን በሁለቱ ተጫዋቾች እንደሚቀርፍ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *