የፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ በተያዘለት ጊዜ ይጀመር ይሆን?

የሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወጣለት ጊዜ መሠረት ላይጀመር እንደሚችል ተገምቷል።

2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ከመጋቢት 1 ጀምሮ እንደሚደረግ የሊግ ኮሚቴ ማሳወቁ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ክለቦች ከተወሰነ እረፍት በኋላ ወደ መደበኛ ልምምዳቸው በመመለስ የውድድሩን ጅማሬ እየተጠባበቁ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመጋቢት 12 በአዲስ አበባ ስቴዲየም ከማሊ ጋር ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የአንደኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ መጋቢት 19 ማሊ ባማኮ ላይ የሚያደርግ ይሆናል። በመሆኑም ለ33 ተጫዋቾች የመጀመርያ ጥሪ ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዩ የካቲት 26 ቀን 08:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቴክኒክ ኮሚቴም ቢሮ በመገኘት ሪፖርት እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል፡፡ ይህ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጥሪ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች በቀጣይ ከሚጠበቃቸው ወሳኝ ጨዋታ አኳያ ከሁለት እስከ ሦስት ተጫዋቾችን ያስመረጡ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ለመልቀቅ እንደሚቸገሩ ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛል። ዛሬም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኞች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ይህ ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር ሰምተናል።

ይህን ተከትሎ የኦሊምፒክ ቡድኑ ከሚጠብቀው ወሳኝ ጨዋታ አንፃር የሊጉ ኮሚቴው መጋቢት አንድ ይጀምራል ብሎ ያወጣው መርሐግብር ወደ ሌላ ጊዜ ሊሸጋሸግ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *