ኢትዮጵያ ከአለም ዋንጫ ምድብ ማጣርያ ውጪ ሆነች

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሩስያ ለምታስተናግደው የ2018 የአለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ለመግባት ከኮንጎ ጋር ባደረገው ጨዋታ በድምር ውጤት 6-4 ተሸንፎ ተሰናብቷል፡፡

በአዲስ አበባ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ 4-3 ተሸንፎ ወደ ብራዛቪል ያቀናው ብሄራዊ ቡድናችን ከአዲስ አበባው ጨዋታ የተወሰኑ ለውጦችን በማድረግ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ በግብ ጠባቂነት አቤል ማሞ ታሪክን ተክቶ ሲገባ ዋሊድ በአስቻለው ፣ ዘካርያስ በነጂብ ሳኒ ፣ ኤልያስ ማሞ በአስቻለው ግርማ እንዲሁም ራምኬል በበረከት ተተክተው በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል፡፡

በመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ በኳስ ቁጥጥር ከኮንጎ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየች ሲሆን ኮንጎዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ የተሸሉ ነበሩ፡፡ ጌታነህ ከበደ በ28ኛ ደቂቃ ኢትዮጵያን መሪ ያደረገች ግብ ያስቆጠረ ሲሆን የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀውም በኢትዮጵያ 1-0 በመሪነት ነው፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ3 ደቂ ውስጥ አምበሉ ፍራንሲስ ንጋንጋ የኮንጎን የአቻነት ግብ አስቆጥሮ የኢትዮጵያን የማለፍ ተስፋ የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ሲከት ከ10 ደቂቃ በኋላ በ58ኛው ደቂቃ ቲዬቪ ባፎውማ ኮንጎን መሪ ያደረገችና የኢትዮያን ተስፋ ያጨለመች ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታውም በኮንጎ 2-1 አሸናፊነት (በአጠቃላይ ውጤት 6-4) ተጠናቋል፡፡

ኮንጎ ኢትዮጵያን ማሸነፏን ተከትሎ በ5 ምድብ ተከፍሎ ለሚደረገው የአፍሪካ ዞን የአለም ዋንጫ ማጣርያ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሃገራትን ተቀላቅላለች፡፡ ወደ ምድብ ከገቡት ሃገራት መካከል ጋቦን ፣ ዩጋንዳ ፣ ጋና ፣ ናይጄርያ ፣ ዛምቢያ ፣ ሊቢያ እና ሞሮኮ ይጠቀሳሉ፡፡

 

ያጋሩ