በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንኛ ዲቪዝዮን የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ የሚገኙት ባንክ፣ አዳማ እና መከላከያ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ወጥ ባለ ሆነ አቋም ላይ የማይገኙት መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማን ረፋድ 04:00 ላይ በመከላከያ የልምምድ ሜዳ ያገናኘው ጨዋታ በመከላከያ 1-0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
የመከላከያ አጥቂ ለሆነችው የሄለን እሸቱ የልደት ቀን የቡድን አጋሮቿ ኬክ በመቁረስ አክብረውላት በተጀመረው ጨዋታ እንግዶቹ ሀዋሳዎች መከላከያዎች ኳሱን አደራጅተው እንዳይጫወቱ በማፈን በሚሰሩት ስህተት በአጥቂያቸው መሳይ ተመስገን አማካኝነት የጎል ዕድል ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት የተመልካቹን ትኩረትን የሚስብ ነበር። በ5ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ ፍጥነቷን ተጠቅማ ወደ ፊት በመሄድ ከሳጥን ውጭ አጥቂዎ መሳይ ተመስገን አክርራ የመታችውን ግብጠባቂዋ ማርታ በቀለ እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣችው አንዱ ማሳያ ነው።
ባለሜዳዎቹ መከለከያዎች ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው ብልጫ ወስደው ቢጫወቱም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ዝቅተኛ ነበር። አማካዮቹ ከአጥቂዎቹ ጋር የነበረው ግኑኝነት የተቋረጠ በመሆኑ ሲሳይ ገብረዋኀድ ካደረገችው የጎል ሙከራ በቀር ሌላ መመልከት አልቻልንም። ሃዋሳዎች በኩል አጥቂዎን መሳይን ፍለጋ ብቻ ያተኮረ አጨዋወት ሌሎች አጥቂዎች ነፃነት መና እና ምርቃት ፈለቀን መዘንጋቱ ቡድኑን እንቅስቃሴ የተገደበ ቢያደርገውም 35ኛው ደቂቃ በአማካይዋ ሳራ ኪዶ ከሳጥን ውጭ የተፈጠረ የግብ አጋጣሚ ተመልክተናል።
ከእረፍት መልስ በሁሉም ረገድ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተመለከትን ሲሆን በአንፃራዊነት በእንቅስቃሴ መከላከያ ብልጫ መውሰድ ችሏል። መከላከያዎች ጎል ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶላቸው 60ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሯ በመግጨት ተከላካይዋ ፋሲካ በቀለ ለመከላከያ ጎል አስቆጥራለች።
በተደጋጋሚ ወደ ፊት ተጭነው ያጠቁ የነበሩት የመከላከያ እንስቶች 66ኛው ደቂቃ ተቀይራ በገባችው የምስራች ላቀው አማካኝነት ከቅጣት ምት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥራ የነበረ ቢሆንም የሀዋሳዋ ግብጠባቂ አባይናሽ ያዳነችባት እንዲሁም ተቀይራ የገባችው ብሩክታይት አየለ ከግራ መስመር ጠርዝ ተከላካዮችን በማለፍ ለመዲና አወል አቀብላት ቺፕ አድርጌ አስቆጥራለው ብላ ኳሱ እረዝሞ ለጥቂት የወጣባት በመከላካዮች በኩል ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሉ እድሎች ነበሩ።
በጨዋታው መጠናቀቂያ አስር ደቂቃዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ የአጥቂነት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ሙሉ ለሙሉ ተጭነው የተጫወቱት እንግዶቹ ሀዋሳዎች ሁለት ጎል መሆን የሚችሉ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎችን አምክነዋል። 82ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን በግራ መስመር ቆርጣ በመግባት መሬት ለመሬት ለጎሉ አንድ ሜትር ርቀት ላይ ብቻዋን ለቆመችው ነፃነት መና አቀብላት በማይታመን መልኩ ወደ ሰማይ የሰደደችው። እራሷ ነፃነት በድጋሚ 86ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ የተጣለላትን ኳስከግብጠባቂዋ ማርታ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ በእግሯ መሐል ኳሱን አሾልካ ገባ ተብሎ ሲጠበቅ በመከላከያ በኩል በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የታየችው አምበሏ ሳምራዊት ኃይሉ በፍጥነት ደርሳ ያወጣችው ኳስ ሃዋሳዎችን አቻ ማድረግ የሚያስችሉ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በመጨረሻም ጦረኞቹ በርከት ባሉ የመከላከያ ደጋፊዎች ታጅበው ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ያደረጉት የመከላከል ጥረት ተሳክቶላቸው 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።
በአዳማ አበበ ቢቂላ 10:00 ላይ በተካሄደውና ቁጥሩ እጅግ በርካታ ተመልካች በታደመበት ጨዋታ አዳማ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
በጨዋታው ጅማሬ በ3ኛው ደቂቃ እፀገነት ብዙነህ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ወደ ጎል መታ የአዲስ አበባዋ ግብጠባቂ ስርጉት ተስፋዬ ወደ ውጭ ያወጣችባት ሙከራ ማየት ብንችልም የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ጨዋታው እየቀዘቀዘ ሊሄድ ችሏል። በዋና አሰልጣኙ መሰረት ማኒ ሳይመራ በሁለት በምክትል አሰልጣኞቹ እየተመሩ የገቡት አዲስ አበባዎች በፈጣን አጥቂዎቻቸው ታግዘው ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም ግብ የማግባት እድል መፍጠር ላይ ድክመቶች ነበሩ። ያም ቢሆን ከሳጥን ውጭ ህይወት ረጉ 17ኛው ደቂቃ የሞከረችው የአዳማ ተከላካዮች ተደርበው ለማውጣት ሲሞክሩ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ታኮ የወጣው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት ብልጫ የነበራቸው አዳማዎች ከመጀመርየው ሙከራ በኋላ 27ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካይዋ ነፃነት ፀጋዬ ያሻገረችውን ሰርካለም ጉታ በግንባሯ ገጭታ የወጣባት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር። ወደ መልበሻ ክፍል ማምሪያ አካባቢ 45ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዮዲት መኮንን በጥሩ ሁኔታ ጎል አስቆጥራ አዳማዎች መሪ መሆን ቻሉ።
ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ብንመለከትም በጠንካራ የጎል ሙከራ ያልታጀበ በመሆኑ ሁለተኛው አጋማሽ ጎሎችን ሳንመለከት ቀርቷል። 53ኛው ደቂቃ የአዳማ የሁለተኛው አጋማሽ ዘመን አዲስ ፈራሚ ሎዛ አበራ ተቀይራ በመግባት መጫወት ችላለች።
ከጨዋታው እንቅስቃሴ ባሻገር ትኩረት ይስብ የነበረው የዕለቱ ዳኞች ከአቅም በታች ማጫወት፣ የወሰኑትን ውሳኔ ከወሰኑ በኋላ የመቀየር ነገር በተደጋጋሚ መመልከት የጨዋታውን መንፈስ ሲረብሽ ነበር ።
በመጨረሻም አዳማዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ አዲስ አበባዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ጥሩ ፉክክር ቢያስመለክቱንም ጨዋታው በአዳማ 1 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በልምምድ ሜዳው ጌዴኦ ዲላን አስተናግዶ 3-1 አሸንፏል። ረሒማ ዘርጋው ሁለት ጎሎችን ስታስቆጥር ሽታዬ ሲሳይ ቀሪውን አስቆጥራለች። ረድዔት አስረሳኸኝ ደግሞ የብቸኛዋ የዲላ ጎል ባለቤት ናት።
ባህር ዳር ላይ ጥረት ኮርፖሬት ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 ሲያሸንፍ አሰላ ላይ ኤሌክትሪክን የጋበዘው ጥሩነሽ ዲባባ በተመሳሳይ 1-0 አሸንፏል። ቀሪው የአርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ነገ የሚካሄድ የ14ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡