የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ሲከናወኑ በምድብ ሀ አካዳሚ፣ አምቦ ጎል እና ድሬዳዋ ሲያሸንፉ በምድብ ለ አዳማ እና ፋሲል ድል አስመዝግበዋል።

ምድብ ሀ

በዚህ ሳምንት መደረግ ከነበረባቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ሦስቱ የተካሄዱ ሲሆን ወደ ይርጋለም ያመራው ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ባለሜዳው ሲዳማ ቡናን 1-0 አሸንፎ ተመልሷል። ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ መከላከያን 2-1 ሲረታ፤ አምቦ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን የገጠመው አምቦ ጎል ፕሮጀክት 3-2 አሸንፏል። ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሌላ ጊዜ የተሸጋገሩ ጨዋታዎች ናቸው።

ምድብ ለ

ጎንደር ላይ ኢትዮጵያ መድንን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ ከእረፍት መልስ ባደረጋቸው ስኬታማ ቅያሪዎች በመታገዝ 2 -1 በሆነ ዉጤት አሸንፏል። ጥሩ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጭነው እና የተሻለ ብልጫ አድርገው የተጫወቱት መድኖች የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ተስተዉሏል። 20ኛ ደቂቃ ላይ ካሳሁን ሰቦቃ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ያዳነበት ጥሩ የሚባል ሙከራ ነበር። በፋሲል ከነማ በኩል የመጀመሪያዉን አጋማሽ የመሀል ክፍሉ ላይ አለመረጋጋት ይስተዋል ነበር። በሙከራ ደረጃ 12ኛ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ያሻገረለትን ካስ ዮናስደሳለኝ ሳይጠቀምበት የቀረዉ የሚጠቀስ ነበር።

የተሻለ ተጭነዉ የተጫወቱት መድኖች በመልሶ ማጥቃት 33ኛዉ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ቢኒያም ፍቃዱ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታውም ኢለማውን የጠበቀ አልነበረም። በድጋሚ በመልሶ ማጥቃት የተገኝውን ኳስ ከብዙነህ አየለ ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኝው ካሳሁን ሰቦቃ ግሩም ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉት እንግዳዎቹ መሪነታቸዉን እንዳስጠበቁ ነበር ወደ እረፍት ያመሩት።

በሁለተኛው አጋማሽ ለዉጦችን አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት ባለሜዳዎቹ የተሻለ ተጭነው በመጫወት 50ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጪ ዳንኤል ፍፁም ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበት የሚጠቀስ ነው። 53ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዣቬየር ሙሉ ሳጥን ዉስጥ ያገኝዉን ኳስ አንድ ተከላካይ አልፎ ድንቅ ግብ በማስቆጠር አቻ መሆን ችለዋል።

በእንግዳው ቡድን በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ
ወደኋላ አፈግፍገው ዉጤት አስጠብቀዉ ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸዉ ቀርቷል። በሙከራ ደረጃ ከቆሙ ኳሶች እና ከ ማእዘን ምት ከተገኙ ኳሶች ወጭ የተሻለ ሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በተደጋጋሚ ወደግብ ቢደርሱም ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ፋሲሎች ተቀይሮ የገባዉ ናትናኤል ማስረሻ የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ትናኤል ማስረሻ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በጭንቅላቱ ገጭቶ ፋሲልን ሙሉ ሶስት ነጥቦች ማስጨበጥ ችሏል።

በሌሎች የምድብ ለ ጨዋታዎች አዳማ ላይ በ8:00 ወልቂጤ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 2-1 አሸንፎ ነጥቡን 16 አድርሶ በመሪነቱ ሲቀጥል ሀላባ ከተማ ከ አሰላ ኅብረት 2-2፤ ኤሌክትሪክ 1-1 አአ ከተማ አቻ ተለያይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *