ማርት ኑይ ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ተመልሰዋል

ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ማርት ኑይ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በድጋሚ ተመልሰዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማን ለክለቡ ባቀረቡት ቅድመ ሁኔታ ከስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ባለፈው ሳምንት በስምምነት ከክለቡ ጋር መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን ክለቡን በ2006 የውድድር ዘመን ያሰለጠኑት ሌላኛው ሆላንዳዊ ማርት ኑይ በድጋሚ ቡድኑን ተረክበዋል፡፡

አሰልጣኝ ማርት ኑይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መስማማታቸውን ተከትሎ አዲስ አበባ በመምጣት የፌዴሬሽን ጉዳዮችን ያጠናቀቁ ሲሆን ክለቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ በይፋዊ መግለጫ የአሰልጣኙን ቅጥር ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የ61 አመቱ ማርት ኑይ በ2006 ቅዱስ ጊዮርጊስን ተረክበው በአንደኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቡን መሪ አድርገው ቢያጠናቅቁም ከታንዛንያ ብሄራዊ ቡድን የቀረበላቸውን የአሰልጥንልን ጥያቄ ተቀብለው ወደ ዳሬሰላም አምርተዋል፡፡ በታንዛንያ ብሄራዊ ቡድን ውጤት ማምጣት የተሳናቸው ማርት ኑይ በጁን 2015 በቻን ማጣርያ በዩጋንዳ በሜዳቸው 3-0 መሸነፋቸውን ተከትሎ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

ማርት ኑይ ከዚህ ቀደም የሞዛምቢክ ብሄራዊ ቡድንን ፣ የቡርኪናፋሶ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን እንዲሁም የደቡብ አፍሪካውን ሳንቶስ አሰልጥነዋል፡፡

ያጋሩ