ለኦሊምፒክ ማጣሪያ የኢትዮጵያ አቻውን የሚገጥመው የማሊ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከአዲስ አበባው ጨዋታ አስቀድሞ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ባማኮ ላይ ከቡርኪናፋሶ አቻው ጋር እንደሚያደርግ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታወቀ፡፡
በቅርቡ በኒጀር በተደረገው የ20ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ከሆነው ቡድን ከ10 በላይ ተጫዋቾችን በመምረጥ እራሱን ያጠናከረው የማሊ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሁለቱንም ጨዋታዎች ከቡርኪናፋሶ ጋር ባማኮ ላይ የካቲት 28 እና መጋቢት 1 ቀን 2011 የሚያደርግ ሲሆን ዓላማውም ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅት እንዲያግዘው እንደሆነ የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በፋንዬሪ ዲያራ የሚመራው የማሊ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ከሁለቱ ጨዋታዎች በኋላ መጋቢት 12 ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ መጋቢት 14 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ይገጥማል፡፡ የመልስ ጨዋታውም ማሊ ባማኮ ላይ መጋቢት 17 ይደረጋል፡፡
በተያያዘ ዜና ብሔራዊ ቡድኑ በቅርቡ ኒጀር ላይ ቻምፒዮን ከሆነው የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከአስር በላይ ለሚሆኑ ታዳጊዎች ጥሪ ማድረጋቸውን አሰልጣኙ ፋንዬሪ ዲያራ አስታወቁ፡፡ የቡድኑ አምበል ክሌሞን ቡባካር ካኑቴ፣ ማማዱ ትራኦሬ፣ ቡባካር ትራኦሬ፣ ፎዴ ኮናቴ፣ ሳምቡ ሲሶኮ፣ ሃጂ ድራሜ፣ ኤልቢላል ቱሬ፣ አማዱ ዳንቴ፣ ሱሌይማን ኩሊባሊ እና አልከሊፋ ኩሊባሊ ጥሪ የተደረገላቸው የአህጉራዊ ሻምፒዮኑ ክለብ አባላት ናቸው፡፡
ከነዚህ ተጫዋቾች በተጨማሪ አሰልጣኙ በውጭ ሃገራት በተለይ በፈረንሳይ ሊግ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ጥሪ ያረጉ ሲሆን ቡድኑ ተሰባስቦ ዝግጅት መጀመሩ ታውቋል፡፡ አሰልጣኙ አክለውም « መጋቢት 12 ወደአዲስ አበባ እናቀናለን በ14 ጨዋታችን ካረግን በኋላ በ15 እንመለሳለን፡፡ ምንም የረፍት ጊዜ የለንም እንደምታውቁት ታዳጊዎቹ ከውድድር ነው የመጡት፣ ከውጭ ከመጡ ተጫዋቾች ጋር አቀናጅተን የተሸለ ነገር ለመሥራት እንጥራለን » ብለዋል፡፡
የማሊ ተጋጣሚ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 33 ተጫዋቾችን ይዞ ዝግጅቱን ባለፈው አርብ የጀመረ ሲሆን የተጫዋቾቹን ቁጥር በቅርቡ ወደ 23 በመቀነስ ለጨዋታው እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡