የኢትዮጵያ እግርኳስ ብሔራዊ ቡድን በምን መልኩ መጠናከር እንዳለበት እና ላሉበት ፈርጀ ብዙ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳቦች ይነሱበታል ተብሎ የታመነበት አሰልጣኞች እና የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የተገኙበት ውይይት ቅዳሜ ተጀምሮ ዛሬ ተጠናቀቀ።
ባሳለፍነው ቅዳሜ በተጀመረው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ እንደተጠበቀው ብዛት ያላቸው አሰልጣኞቹ ያልተገኙ ሲሆን በመክፈቻ ንግግር የጀመሩት የዕለቱ የክብር እንግዳ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ “በጋራ መስራት አለብን፤ የብሔራዊ ቡድናችን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ሊሆን ይገባል። እንደዚህ ዓይነት መድረኮች ያስፈልጋሉ። እርስ በእርስ ያለው መገፋፋት ታሪክ ሆኖ ሊቀር ይገባል” ብለዋል።
በመቀጠል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በብሄራዊ ቡድናችን ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለታዎችን በማንሳት በጀመረ ንግግራቸው ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የሚያስችሉ ሁኔታዎች በሚል የእግር ኳስ ባህል ማዳበር ፣ የህዝብ ብዛት ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ፣የተጫዋች ጥራት ፣ የአሰልጣኞች እና ስልጠና ጥራት፣ የሊግ ውድድር ጥራት የክለቦች አወቃቀር ከኢትዮጵያ ውጭ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ደረጃ እና የብሔራዊ ቡድን አስተዳደር ጠንካራ ብሔራዊ ቡድንን ይፈጥራል በማለት ተናግረዋል።
ተመሳሳይ የሆኑ ጥናቶች በቴክኒክ ዳሬክተሩ መኮንን ኩሩ እና የስፖርት ሳይኮሎጂ ሳሙኤል ስለሺ ሃሳቦች የቀረበ ሲሆን በማስከተል የጉባኤው ተሳታፊ በሆኑት አሰልጣኞች በኩል እንዲህ ያለ መድረክ መዘጋጀቱን አመስግነው ከዚህ በታች የተዘረዘሩ የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን አንስተዋል።
– ክለብ ሳይኖር ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መጠበቅ ከባድ ነው። ከተጫዋቾች የፊርማ ገንዘብ ጋር የአሰልጣኞች ስም ይያያዛል ከእንደዚህ ዓይነት ተግባሮች ብንወጣ መልካም ነው።
– የግብ ጠባቂዎች ላይ ምን እየተሰራ ነው። ስንት የውጭ ሀገር ተጫዋች በአንድ ቡድን መጫወት አለበት? የሚለው ህግ በደንብ እንደገና መፈተሽ አለበት።
– ለብሄራዊ ቡድን የተሻለ አቅም ያላቸው አይመረጡም። ለምሳሌ ከ2005 ጀምሮ ብሄራዊ ቡድን የሚጫወት አለ። እሱን የሚተካ ተጫዋች ጠፍቶ ነው? በጭፍን መምረጥ ይቁም።
– እርስ በእርስ ያለን መከባበር ምን ያህል ነው? አንድ ቡድን ውስጥ ያሉ ሙያተኞች እርስ በእርስ ለመጠላለፍ ነው የሚያስቡት።
– በዚህ ዓመት ከ17 ዓመት በታች የተጫወተ የሚቀጥለው ዓመት ከ20 ዓመት በታች ይጫወታል ወይ? ቅብብሎሽ ሊኖር ይገባል። ተጫዋቹ የሚፈልገውን እያሰራን ነው። እኛ የምንፈልገውን ወይም እግር ኳሱ የሚጠይቀውን አይደለም የምናሰራው።
– ኢትዮጵያ በፊፋ ወርሃዊ ደረጃ ያለችበት ቦታ እግር ኳሳችንን የሚገልጽ ነው። የወደቅነው ከተለምዷዊ አሰራር ባለመውጣታችን ነው። ብዙ ሀገራት ጥለውን ሄደዋል።
– የዛሬ ስንት ዓመት የተጫዋች ፂም እያስላጨን ወጣት ቡድን ብለን ፓስፖርት እያስቀየርን ይዘን ሄደናል። አሁን ኳሳችንን የገደለው እሱ ነው።
– ይህ መድረክ ለሚዲያ ፍጆታ እንዳይሆን ስጋት አለኝ። በደንብ ልንሰራበት ይገባል። የጀመራችሁት ነገር እንደ ዲፓርትመንት ሊዋቀር ይገባል።
– የድሮ አሰልጣኞች ለሙያቸው ሟቾች ናቸው። ዲሲፕሊን ወሳኝ ነው።
– ኳስ ተጫዋች ስለነበር አሰልጣኝ ይሆናል ማለት አይደለም፤ እንዲሁም ማስተርስ አለው ማለት አሰልጣኝ ይሆናል ማለት አይደለም።
– ስራ አስፈጻሚው የቡድን መሪ እየሆነ ተጋጭተናል። የቡድን መሪ መሆን ያለበት ባለሙያው ነው። ስለ አሁን ሳይሆን ስለ 8 ዓመት ነው ማቀድ እና መስራት ያለብን። እግር ኳስ ልማት ነው፤ ስለሆነም የፊቱን ማሰብ አለብን። ወድቀናል ስለ ወደፊቱ አቅደን መስራት አለብን።
– ተጫዋች ሊመራን አይገባም። እሱ ስራው መጫወት እና የእኔን ትዕዛዝ መቀበል ነው ያለበት። እከሌ ይግባ አይግባ እሱን ምንም አያገባውም።
– እዚህ ያለው አሰልጣኝ በየክለቡ ዋስትና የለውም። ዋስትና የሌለው አሰልጣኝ ደግሞ ስለቆይታው እንጂ ሌላ ላይሰራ ይችላል። ይህ ተጽዕኖ ብሄራዊ ቡድኑ ላይ ይመጣ።
– ተጨዋቾች በአንድ ክለብ ተረጋግተው አይቆዩም። አሰልጣኞችም እንደዚሁ አይቆዩም። ስለሆነም ለሀገር ተጨንቀው እንዳይሰሩ ምክንያት እየሆነ መጥቷል።
– ለአንድ ቡድን ውጤታማነት ወጥነት ያለው አሰራር ወሳኝነት አለው። የአሰልጣኞች ደረጃ መውጣት አለበት። ፕሪምየር ሊግ ላይ ማሰልጠን ያለበት ማን ነው? የሚለው ግልጽ ደረጃ መኖር አለበት።
– እንዲህ ዓይነት መድረክ ለክለብ አመራሮች መሰጠት አለበት። አመራሮች ሲባሉ ፕሬዝዳንቶች እና ውሳኔ በክለቡ የሚሰጡ አካላት መኖር አለባቸው።
– የእድሜ ደረጃ ብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች መኖር አለበት።
– አሰልጣኞች ገብተው ሊያነቡ የሚችልበት ላይብረሪ ወይም አዳዲስ ነገሮችን የሚቀስሙበት ቦታ የለም። ይህ መስተካከል አለበት። የሚሰጡት ስልጠናዎች ሁሉም ገብቶ የሚወጣበት መሆን የለበትም።
– አሰልጣኞች ለህሊናችን እንኑር። ታዳጊዎች ለማፍራት እንሞክር። ከዚህ በኋላ ለሀገር ምንም ሳንሰራ ማለፍ የለብንም። አብረን እንስራ።
በመቀጠል ከጉባዬው መሪዎች ምላሽ በመስጠት የመርሐግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።
ዛሬ በቀጠለው ከቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጋር በተደረገው ሰፊ ውይይት እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ካደረጉ በኋላ፤ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል በንግግራቸው ከዚህ ውይይት ምን እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ የቀድሞ ተጫዋቾች አሁን ያለው ብሄራዊ ቡድናችንን በምን መልኩ ማጠናከር እንደሚገባው ልምዳቸውን እና እውቀታቸውን እንዲያካፍሉ የሚያስችል መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል። በመቀጠል ከተሳታፊዎቹ በርከት ያሉ ጠቃሚ ሀሳቦች ተነስተዋል ከነዚህ መካከል:-
– በእኛ እና በሌሎች ሀገራት መካከል ያለው ልዩነት በስፖርት ሳይንስ ሰፍቷል፤ መጥበብ አለበት።
– አሰልጣኞች የገቡበት የገንዘብ ቅብብል በማያዳግም ሁኔታ እርምጃ በመውሰድ ፌዴሬሽኑ ሊያስቆመው ይገባል።
– ተጫዋቾች በራሳቸው ፍልስፍና አራማጆች ሆነዋል። የአንተን ልተገብር ስትል እንደ አሰልጣኝ ትቸገራለህ። እነዚህ ተጫዋቾች በቡድኑ አጨዋወት ውስጥ መግባት አለባቸው።
– ከታች ጀምረን እንስራ ሲባል ታች የሚሰሩት አሰልጣኞች አቅም ምን ያህል ነው የሚለው መታየት ይገባዋል።
– አሰልጣኞች በየጊዜው ከዘመናዊ እግርኳስ ጋር ራሳቸውን የሚያዛምዱበት ስልጠና ማግኘት አለባቸው፣ ዓለም በየጊዜው ተለዋውጧል።
– ከ31 ዓመት በኋላ ያለፈው ብሄራዊ ቡድን ህብረት እና አንድነት አሁን ላለው ለብሔራዊ ቡድናችን ምሳሌ መሆን የሚችል ነው።
– አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ህብረት የለውም፤ በደንብ መስራት አለበት።
– ለአሰልጣኞች ጊዜ እየተሰጠ አይደለም። ይህንን በፌዴሬሽኑ ክለቦች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት።
– የቀድሞ የብሔራዊ በድን ስብስብ ማኅበር ቢኖር ጥሩ ነው።
– ስልጠና ሲመጣ ብሔራዊ ቡድን ተጫውተው ላለፉ ቅድሚያ ቢሰጥ ጥሩ ነው።
– ጥናታዊ ጽሁፍ ሲዘጋጅ እኛንም ቢያሳትፍ ጥሩ ነው።
– ብሔራዊ ቡድናችን ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ብናደርግ ጥሩ ነው። የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር እኛ የበኩላችንን ድጋፍ ማድረግ እንፈልጋለን።
– ወደ እግርኳሱ ሚመጡ አመራሮች የስፖርት ቋንቋን የሚያውቁ መሆን አለባቸው ምንም ልንግባባ አልቻልንም።
– እግርኳሱ ላይ ያለው የገንዘብ ቅብብሎሽ ጉቦ በዝቷል ሊቆም ይገባል።
– ውድድሮች እንደድሮው ወደ ቀበሌ መምጣት አለበት።
– ብሔራዊ ቡድናችን በሜዳው እየተሸነፈ ነው ከዚህ በፊት ይህ አልነበረም ጥናት ያስፈልገዋል። የሚሉ ሃሳቦች ተነስተውበት በመጨረሻም ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ” የሰጣችሁትን ሀሳብ ተቀብለናል፤ እናመሰግናለን። ያነሳችሁትን ሁሉ ተቀብለን በስነድ መልክ አዘጋጅተን ለውይይት እንጠራችኋለን።” በማለት ውይይቱም በዚሁ መልክ ተጠናቋል።
©መረጃውን ያገኘነው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ህዝብ ግኑኝነት ነው።