የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ጀመረ


መጋቢት 12 ለቶኪዮ ኦሊምፒክ አንደኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ከማሊ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርገው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ዝግጅቱን ጀምሯል።

በመጀመርያው ጥሪ ለ33 ተጫዋቾች ባሳለፍነው ሳምንት ጥሪ ያደረጉት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዛሬ በይፋ ከ09:30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም በመገኘት ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

በዛሬው የልምምድ መርሐግብር ላይ ጥሪ ከተደረገላቸው 33ቱም ተጫዋቾች የተገኙ ሲሆን አሚን አህመድ የተባለ በሀገር እንግሊዝ የሚኖር በታችኛው ዲቪዚየን (Mousehle AFC) የሚጫወት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከቡድኑ ጋር የተካተተ ሌላ ተጫዋች ሆኗል። በዛሬው ዕለት ሁለት ሰዓት በቆየው ልምዳቸው በግማሽ ሜዳ ለሁለት ተቧድነው እንዲጫወቱ በማድረግ ተጫዋቾቹ አሁን ያሉበትን ደረጃ ለማየት ተሞክሯል።

ከልምምዱ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ” የመጀመርያው የልምምድ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ አስር ተጫዋቾችን እንቀንሳለን። የቀሩት ሃያ ሦስት ተጫዋቾች ከማሊ ጋር በሚኖረን የደርሶ መልስ ጨዋታ ከቡድኑ ጋር አብረው የሚቆዩ ይሆናል። ሲጠናቀቅ የምናሳውቀው ቢሆንም ከማሊ ጨዋታ አስቀድሞ ሁለት አልያም አንድ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማግኘት እየተነጋገርን ነው፤ እንደተጠናቀቀ እናሳውቃለን። ” ብለዋል። አክለውም ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት እንደፈተና እየተወሰደ ያለውና በመሐል ለሚደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ተጫዋቾቹ ወደየክለባቸው ያመራሉ ለሚለው ጥያቄ ” ተጫዋቾቹን አንለቅም፤ ከእኛ ጋር አብረው ይቆያሉ ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *