የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር የውድድር አፈፃፀም ሪፖርት እና ግምገማ የክለቦቹ አመራሮች እና የፌዴሬሽኑ ተወካዮች በተገኙበት በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ተደርጓል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ በፌዴሬሽኑ የሚገኙ የውድድር አደረጃጀት ኃላፊዎች፣ የአስራ ስድስቱ ክለቦች ተወካዮች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው በዚህ መርሐግብር ላይ የእንኳን ደህና መጣቹ ንግግር የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከተደረገ በኋላ ተጀምሯል።
በመቀጠል የ2011 የአንደኛው ዙር አፈፃፀምን አስመልክቶ በሊግ ኮሚቴ ዳይሬክተር አቶ ከበደ አማካኝነት ሪፖርት ቀርቧል። በሪፖርታቸውም ከፌዴሬሽንና ከክለቦች በተወጣጡ ባለሙያዎች የሊግ ኮሚቴ መቋቋሙን እና በትግራይ እና በዐማራ ክለቦች መካከል የነበረውን ችግር በመፍታት ውድድሩን ያለምንም ችግር በየሜዳቸው በሰላም ለማከናወን መቻሉን ከገለፁ በኋላ ወደ ቁጥራዊ መረጃ ያመሩ ሲሆን በአንደኛው ዙር በተካሄዱ ጨዋታዎች በጥቅሉ 457 የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርዶች 16 ቀይ ካርድ መሰጠታቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በስፖርታዊ ጨዋነት በኩል በተሻለ ነጥብ ያመጡት ክለቦች በወጣላቸው ደረጃ መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ9,04 አንደኛ ፣ ጅማ አባጅፋር 8,96 ሁለተኛ ፣ አዳማ ከተማ 8,88 ሦስተኛ ደረጃ ሲይዙ ስሑል ሽረ በ8,66 የመጨረሻ ደረጃን ይዟል።
በሊግ ኮሚቴው በአንደኛው ዙር የተከናወኑ ጠንካራ ተግባሮች ተብለው የተገለፁት ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ለዳኞች እና ለኮሚሽነሮች ስልጠና መሰጠቱ፣ የፀጥታ ኃይሎች በየሜዳው ያደረጉት ክትትል በጣም ጥሩ መሆኑ፣ ክለቦች በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ የሜዳ ገቢ ማግኘታቸው፣ የኮሚኒኬ ዝግጅት እና ስርጭት በኢሜይል መከናወኑ ሲጠቀስ የነበሩ ደካማ ጎኖች ደግሞ ተተኪዎች በተፈለገው ደረጃ ያለማግኘት በተለይ የግብጠባቂዎች ችግር፣ አንዳንድ ተጫዋቾች ደጋፊዎች የዳኛን ውሳኔ በፀገ አለመቀበል፣ የመወዳደሪያ ሜዳዎች በተሟላ መልኩ ማግኘት አለመቻል የሚሉ ናቸው።
የወደፊት የትኩረት አቅጣጫን በተመለከተ የ2ኛው ዙር የወንዶች ፕሪምየር ሊግ በተያዘለት መርሐግብር መሰረት እንዲከናወን በትኩረት መስራት፣ ፕሮግራሞች ተስተካካይ ሳይሆኑ እና ሳይቀየሩ በወጣለት መርሀግብር መሰረት እንዲከናወኑ በትኩረት ማዘጋጀት፣ የደጋፊ ማኅበራት የክለቡን ዓላማ ለማሳካት መስራት እንጂ ከተቋሙ በላይ በመሆን በጉልበት ውድድሮች እስከማቋረጥ እርምጃ መውሰድ ድረስ መሄዳቸው የታየ በመሆኑ ክለቦች የደጋፊዎቻቸውን መተዳደርያ ደንብ በመፈተሽ አሰራራቸውን እንዲያስተካክሉ ቢደረግ የሚሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጠው ንግራቸውን አጠናቀዋል።
በማስከተል የዳኞች ኮሚቴ የአፈፃፀም ሪፖርት አቶ ፍቃዱ ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርታቸውም በቅድመ ዝግጅት ለዳኞች በሁሉም ደረጃ ውድድር ለመምራት የሚያበቃ የንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የተነደፈ የአካል ብቃት ፈተና እንዲፈተኑ መደረጉን ገልፀዋል። በውድድር ወቅት በተከናወኑ ተግባሮች በዋና ዳኝነት ከፍተኛ ነጥብ ያገኙ 7 ዝቅተኛ ነጥብ ያመጡ 3፤ በረዳት ዳኞች ከፍተኛ 7 ዝቅተኛ 4 ጨዋታዎችን የመሩ ናቸው። በአጠቃላይ 480 የእግርኳስ ዳኞች ምደባ ተከናውኗል።
በውድድር ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ዳኞችን በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት እንደልብ አለመመደብ፣ በቂ የፀጥታ ኃይል አለመኖር እና የዳኞች ከለላ አለመስጠት። የዳኞችን የጨዋታ አፈፃፀም በተመለከተ ከጨዋታ ታዛቢዎች የሚቀርቡ ሪፖርት የተሟላ፣ የተብራራና የውድድሩን አፋፃፀም በትክክል የማይገልፅ መሆን፣ የጨዋታ ህግ መዛባት በፈጠረ የጨዋታ አመራር ላይ የአንድ አመት ከ6ወራት ቅጣት መጣሉን ገልፀዋል።
በመቀጠል ከተሳታፊ ክለቦች በቀረቡ ሪፖርቶች ዙርያ ከክለቦች በኩል አስተያየቶች ቀርቧል።
መቐለ 70 እንደርታ (አቶ ሽፈራው)
በዐማራና በትግራይ በክለቦች መካከል ውድድሮች እንዲካሄዱ መወሰኑ ለፌዴሬሽኑ አመራሮች ለፋሲል እና ለባህርዳር ከነማ አመራሮች ፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ትልቅ አድናቆት ይገባችኋል።
በዳኝነት አመዳደብ በደንብ መፈተሽ አለበት። ዳኞች እየተከበሩ አይደለም፤ ህጎች እየተከበሩ አይደለም፤ ይህ ይታሰብበት ይገባል።
የውድድር ቀንና ሰዓት በስራ እና በትምህርት ቀን መሆኑ ገቢዎችን እያጣን ነው። ጨዋታዎች በእረፍት ቀን እና 10:00 ቢሆን
ኮሚሽነሮች የሙያውን ስነ ምግባር ላይ ቢሰራ መልካም ነው
ቴክኒካል ቦታ ላይ የማይመለከታቸው አካላት አራተኛ ዳኛ እና የመስመር ዳኞችን ተፅዕኖ ውስጥ እየከተቱ በመሆኑ ይህ ስርዓት ሊበጅለት ይገባል።
ሲዳማ ቡና (አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ)
በዐማራ እና በትግራይ ክለቦች መካከል በሜዳቸው እንዲጫወቱ መደረጋቸው የሚደነቅ ቢሆንም በሲዳማ ቡና እና በወላይታ ድቻ መካከል በሜዳቸው እንዲጫወቱ ጥረት ያለመደረጉ ምክንያት ምንድነው?
ውድድሩን ጤናማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከደጋፊ ማኅበራት ጋር ፌዴሬሽኑ ውይይት ቢያደርግ
በዳኝነት በኩል የተሻሉ ነገሮች መመልከት ችለናል
ባህርዳር ከተማ (አብርሃም አሰፋ)
የሽረ እና የባህርዳር ጨዋታ በማናውቀው ምክንያት መቀየሩ ለምንድነው?
የዳኝነት ችግሮች አሉብን። በሜዳችንም ከሜዳችን ውጭም ይህን ለማስተካከል ምን አስባችኋል?
ኳስ እና ፖለቲካ አልተለያዩም። ፌዴሬሽኑ ይህን እንዴት ያየዋል። እኛ በዚህ ረገድ ያጋጠመን ችግር አለ።
ወላይታ ድቻ (አሰፋ ሀሲሶ)
ስፖርት ለፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን የለበትም። ስፖርት የተራራቁትን ማቀራረቢያ ነው። በሲዳማ ቡና በኩል መሰራት የነበረበት ባለመሰራቱ ነው ውድድሩ ወደ አዲስ አበባ የመጣው እንጂ እኛ በሜዳችን ለመጫወት ፍቃደኛ ነን። በቀጣይ ይህ ነገር መስተካከል አለበት።
የዳኝነት ሁኔታ ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ነው። ለዳኞች ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል።
በዘንድሮ ውድድር በሜዳቸው የሚጫወቱ ቡድኖች ፍፁም ቅጣት ምት በብዛት እያገኙ ነው። ከሜዳቸው ውጭ ሲጫወቱ ግን ፍፁም ቅጣት ምት እያገኙ አይደለም። ይህ ጥናት ሊጠና ይገባል። ዳኞች በደጋፊዎች ጫና ውስጥ እየገቡ ነው።
ለዳኞች የሚሰጠው ስልጠና በተለምዶ ነው። በሜዳ ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን በቪዲዮ ራሳቸውን እየተመለከቱ ከስህተታቸው እንዲማሩ ማድረግ ቢቻል።
ከወልዋሎ (አቶ አብርሃም)
ዳኝነት ላይ ችግር ይኖራል። ሆኖም ዳኞችን ከመውቀስ ይልቅ ራሳችን የምንፈጥራቸውን ችግሮች እናስተካክል።
የጨዋታ ኮምንኬ በሰዓቱ አይደርሰንም። መዘግየት አለ
ስለ ብሔራዊ ቡድን እናስብ። ሊጉ በውጭ ግብ ጠባቂዎች እየተወረረ ነው። ወደ ፊት የሀገር ውስጥ በረኞችን ማግኘት ያስቸግራል። ይህ ሊታሰብበት ይገባል።
አዳማ ከተማ (አንበሴ መገርሳ)
የፀጥታ ችግር የእግርኳሱ የወደፊት ችግር ስለሆነ ስራ መሰራት አለበት።
ለምስጉን ደጋፊዎች የማበረታቻ ሽልማት ቢሰጥ
ከ17 አመት በታች ውድድር መቅረቱ ተገቢ አይደለም። ውድድሩ የሚቀጥልበት መንገድ መፈጠር አለበት።
ለተጫዋች የደሞዝ ክፍያ ሊታሰብበት ይገባል። የክለቦችን አቅም እየተፈታተነ ነው። የምናገኘው ገቢ እና የምናወጣው ወጪ ተመጣጣይ ሊሆን አልቻለም። ፌዴሬሽኑ መፍትሔ ይስጠን።
ፋሲል ከነማ (አቶ ጋሻው)
ውድድሩ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው በሁለተኛው ዙርም በዚሁ ይቀጥል። የሚቀጥለው ዓመት ውድድሩ የተሻለ እየሆነ ይመጣል።
ዳኞች ጫናን መቋቋም የሚችል ሥነ-ልቦና ሊኖራቸው ይገባል። ዳኞች ሲያጠፉ መቅጣት ብቻ ሳይሆን ተጎጂ ክለቦች የሚጠቀሙበት መንገድ ይፈጠር
ውድሮች ሳይቆራረጡ መቀጠል አለባቸው
ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሰለሞን በቀለ)
ፌዴሬሽኑ ወደ ስራ ከመግባቱ አስቀድሞ የሪፎርም ስራ ሰርቶ ወደ ትግበራ መግባቱ ትልቅ ቁም ነገር ነው።
በፕሮግራም መቆራረጥ በተጫዋቾች ላይ የአቋም መለዋወጥ አምጥቶብናል። በቀጣይ ይስተካከል።
የፀጥታ አካላት የሚወስዱት ያልተመጣጠነ እርምጃ ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ በመሆኑ ሊቆም ይገባል። የፀጥታ አካላት ከፌዴሬሽኑ በላይ በውድድሩ ላይ ውሳኔ እየሰጠ ነው። ጭራሽ ደጋፊዎቻችን ወደ ስቴዲየም እንዳይመጡ በፖሊስ ጣቢያ ቤተሰቦች እየተጠሩ እንዲፈርሙ እየተደረገ ነው። ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
በዳኝነት ብቃቱ ቅጣት አንድ ዓመት ከስድስት ወር የተጣለበት ዳኛ እንዴት ኮሚሽነር ይሆናል። የኮሚሽነርነት መስፈርቱ ምድነው?
የትኬት አሻሻጭ ሁኔታ ላይ ችግር አለ። ትኬት ለመሸጥ ከስምምነት የደረሰው ተቋም ከአንድ ተመልካች አራት ብር የሚወስደው በምን አግባብ ነው። መታረም አለበት፤ በተደጋጋሚ ተናግረናል፤ መልስ አላገኘንም።
ኢትዮጵያ ቡና (ስንታየሁ በቀለ)
ውድድሮች በፍጥነት እና ሁሉም በአንድነት መጨረስ አለባቸው። አንዱ አስራምስት ተጫወቶ ሲጨርስ ሌላው ስድስት የሚጫወትበት ሁኔታ መቆም አለበት
ለውጭ ሀገር የተጫዋቸች እና አሰልጣኞች የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ እየሆነ ነው። ሀይ ባይ ያስፈልገዋል።
ከመቐለ ጋር ባደረግነው ጨዋታ በሰላም እንደተጠናቀቀ በሪፖርቱ መቅረቡ ተገቢ አይደለም። ሙሉ ዘጠና ደቂቃ የደረሰብን የስድብ ናዳ የሚታወቅ ነው። ሪፖርቱን አንቀበለውም።
ከክለብ ተወካዮች በመቀጠል በቀረቡት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ዙርያ ምላሽ ተሰጥቷል።
የዳኞች ኮሚቴ ሰብሰቢ ዮሴፍ ተስፋዬ
ክለቦች እኛ ጋር ያለውን ችግር እንፍታ ራሳችንን ማየት አለብን። ዳኞች ሊሳሳቱ ይችላሉ። በዳኝነት በኩል የዘንድሮ መልካም እንደሆነ መሻሻል እንደታየበት መናገራችሁ ባለፉት ዓመታት በዚህ ቦታ እንዲህ ያለ መድረክ ላይ ሲነገር ሰምቼ አላውቅም። ይህ ለእኛ የበለጠ እንድንሰራ የሚያደርገን በመሆኑ አስደስቶናል። በመቀጠል አሁንም በዳኝነቱ ላይ ያልሰራናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ስህተት ስናገኝ የማያዳግም እርምጃ ወስደናል። ከዚህም በኋላ ይህን አጠናክረን እንቀጥላለን። ጫናን ተቋቁመው የሚወጡ ዳኞችን ለመፍጠር በእውቀቱም በየተሻለ ህግ የመተግበር አቅም ያላቸውን ዳኞችን ለማብቃት ከዚህ ቀደም የሚሰጠውን ስልጠና እና የአቃል ብቃት ፈተና አጠናክረን እንሰጣለን።
ኮሚሽነሮች የሚፅፉት ሪፖርት ብዙም አስደሳች አይደለም። አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ስራ መስራት አለብን። በእኛ በኩል በዳኝነት ለሚፈጠሩ ችግሮች ለውሳኔ ፣ ህግ ለማስከበር ቆርጠን ተነስተናል። በህጉ መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን ።
በሁለተኛው ዙር በተጠናከር ሁኔታ እንሰራለን። እናተም ለሆቴል፣ ትራንስፖርት እያላቹ ዳኞችን በኢትዮጵያዊ እንግዳ ጋባዥነት ለመቀበል እንደሆነ ብንረዳም ይህን አቁሙ። ከዚህ ይልቅ የፀጥታ አካላት በበቂ ሁኔታ እንዲመደቡላቸው አድርጉ።
አሁን የዳኝነት ስልጠና አቁመናል አዲስ የተሻሻለውን የዳኝነት ህግን በአማርኛ እየተተረጎመ ነው። በቅርቡ ስልጠና እንጀምራለን፣ የሥነ-ልቦና ባለሙያም አምጥተን የምናስተምር ይሆናል።
ኢሳይያስ ጂራ
ከባለፈው ዓመት የተሻለ መሆኑን ለፌዴሬሽኑ የሰጣችሁን ግብዓቶች፣ ያሳያችሁን ድጋፍ ቁርጠኛ ለመሆናቹ ማሳያ ነው። የዲሲፕሊን ግድፈት የሚወሰነው ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ የሚወስን መስሏቹ የምታስቡ አላችሁ። ይህ የግንዛቤ ስህተት ነው። የህግ ክፍሎች በሚወስኑት ውሳኔ እኛ ጣልቃ ገብተን አናውቅም። ወደፊትም አንገባም። የእኛ ድርሻ በእርግጠኝነት የምንነግራቹ ህግን ማስከበር ብቻ ነው።
በሲዳማ እና በወላይታ ድቻ ቡድኖች ጨዋታ ዙርያ ብዙ ርቀት አልሄድንም። አሁን ከክልሉ ፕሬዝደንት ጋር እየተነጋገርን ነው። የጀመርናቸው ነገሮች አሉ፤ እንደጨረስን እናሳውቃለን።
ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እየተነጋገርን ነው። መታረም ያለባቸው ነገሮች ይታረማሉ። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ ጉዳዩን አናውቅም። ሆኖም የምንከታተለው ይሆናል።
ከትኬት ጋር ተያይዞ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከትኬት ገቢ አታገኙም ነበር። አሁን ጨዋታ ባደረጋቹ በሁለት ቀናት ውስጥ ገቢ እየተደረገ ነው። ይህ ጥሩ መሻሻል ነው። ከትኬት ተቋሙ ጋር በተያያዘ ችግሮች አሉ። ሆኖም ውል ስላለን እንደዚሁ ዝም ብለን ውል አናቋርጥም። ውሉ ሲጠናቀቅ ከእናተ ጋር እንነጋገራለን።
የውጭ ተጫዋቾችን በተመለከተ በቁጥሩ ጉዳይ በሸበሌ ሆቴል ወስነን ወጥተናል። ይህ የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅ ወዴት መሄድ እንዳለብን እንነጋገራለን።
በተጫዋች ዝውውር ወጪ እና ገቢያችን አልተመጣጠነም ያላችሁትን እናንተው ራሳቹ ቁጭ ብላችሁ ነው መፍታት ያለባችሁ። እኛ መድረኩን አመቻችተን እንጠራችኋላን።
ዐወል አብዱራሂም
ሽልማትን በተመለከተ ዘንድሮ ብዙ የምናስተካክላቸው ነገሮች አሉ። ቋሚ የሆነ ዋንጫ፣ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት እናደርጋለን።
አንደኛው ዙር በአንፃራዊነት በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል። በሁለተኛው ዙር ውድድሮችን በወጣው መርሐ ግብር መሰረት እናጠናቅቃለን። ግልፅነት እና ፍትሀዊነት የሰፈነበት በውድድር እንዲኖር እናደርጋለን። እግርኳሳዊ ያልሆኑ ድባቦች አሉ። አመራሮች ደጋፊዎች እግርኳሳዊ መንፈሶች በሜዳዎቻችን እንዲኖሩ ማድረግ ይገባችኋል።
መጋቢት 7 ጀምረን ሰኔ 9 ውድሩን ለማጠናቀቅ አስበናል። ከእኛ ውጭ የሆኑ ችግሮች ካላጋጠሙን በቀር። ከዚህ ባሻገር መስተካከል ያለባቸው ደንቦች አሉ። እነርሱ ላይ ማሻሻያ እናደርጋለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡