ዳዊት ፍቃዱ በጉዳት ከሴካፋ ውጪ ሲሆን ስዩም እና ታሪክ በነገው ጨዋታ ላይሰለፉ ይችላሉ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነገ በ12፡00 ከሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር የመጀመርያ የሴካፋ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ቡድኑ ከአለም ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ መልስ የሴካፋ ዝግጅቱን ትላንት የጀመረ ሲሆን ከተመረጡት 23 ተጫዋቾች መካከል ዳዊት ፍቃዱ በልምምድ ላይ አልተገኘም፡፡ ታሪክ ጌትነት እና ስዩም ተስፋዬ ደግሞ በልምምድ ቦታው ቢገኙም ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰሩ አልታዩም፡፡

ዳዊት ፍቃዱ በብራዛቪል ከኮንጎ ጋር በተደረገው ጨዋታ በ2ኛው አጋማሽ በጉዳት ተቀይሮ የወጣ ሲሆን ከደረሰበት የጡንቻ መሸማቀቅ ለማገገም እስከ 3-4 ሳምንት ድረስ እረፍት እንደሚያስፈልገው ታውቋል፡፡ በአሁኑ ሰአትም ከቡድኑ ጋር በሆቴል አይገኝም፡፡ ይህም ከነገ ጀምሮ እስከ ህዳር 26 ከሚቆየው የሴካፋ ውድድር ውጪ ያደርገዋል፡፡

የቡድኑ አምበል ስዩም ተስፋዬ እና ታሪክ ጌትነትም ከቀላል ጉዳታቸው አገግመው በነገው ጨዋታ የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን በህክምና ባለሙያዎቹ ውሳኔ የመሰለፍ እና ያለመሰለፋቸው ጉዳይ ይወሰናል ተብሏል፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች ተጫዋቾች የማይሰለፉ ከሆነ አቤል ማሞ እና አዲሱ ተስፋዬ ተክተዋቸው ይሰለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቡድኑ ትላንት 10፡00 እንዲሁም ዛሬ ረፋድ ላይ ልምምዱን ሲያደርግ በሁለቱም ቀን ልምምድ ቡድኑ በተመሳሳይ ለሁለት ተክፍሎ በመጫወት ሲለማማድ ታይቷል፡፡

ያጋሩ