አአ U-17 | ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ ሐሌታ እና ኤሌክትሪክም አሸንፈዋል

በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሐሌታ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ አሸንፈዋል።

በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ከተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች መካከል 03:00 ላይ ሐሌታን ከሠላም ያገናኘው ጨዋታ በሐሌታ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ብዙም ሳቢ ባልሆነ እንቅስቃሴ እና መሐል ሜዳ ላይ ተገድቦ በተጠናቀቀው ጨዋታ ሐሌታዎች ከእረፍት መልስ 79ኛው ደቂቃ በዕለቱ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በታየው የቡድኑ አምበል ይስሐቅ መኩርያ የቅጣት ምት ጎል አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።

05:00 በቀጠለው ሌላኛው የዚህ ሜዳ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ከወጣቶች አካዳሚ 0 – 0 ተለያይተዋል። በጨዋታው በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ እና ጠንካራ የጎል ሙከራ መመልከት ብንችልም ጎልና መረብን የሚያገናኝ አጥቂ ባለመኖሩ ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

07:00 በርከት ባለ ተመልካች ታጅቦ የተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በፈረሰኞቹ 3 -2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለወትሮም በየትኛው የዕድሜ እርከን ሁለቱ ቡድኖች በሚገናኙበት ወቅት የሚኖረው ጠንካራ ፉክክር ዛሬም ኃይል የተቀላቀለበት እና በጎል ሙከራ የታጀበ ጠንካራ ፉክክር አይተንበታል። በጨዋታው ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሱፍቃድ ገኑ አማካኝነት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአላዛር ሳሙኤል የቅጣት ምት የመጀመርያ ጎል እና በፀጋዬ መላኩ ሁለተኛ ጎሎች ታግዘው መምራት ችለዋል።

ከእረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በሐብታሙ ጌታቸው ጎል አቻ መሆን ቻሉ። በጨዋታው ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ፈረሰኞቹ ወደ ፊት ተስፋ እንደሚጣልበት በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አካዳሚ እና በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ላይ የታየው በዛሬው ዕለትም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል መልካም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አቤል ዮናስ የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት 3-2 ተጠናቋል።

በጎፋ ሜዳ በተካሄዱ ሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች መከላከያ ከ አዳማ ከተማ 2-2 ሲለያዩ ኤሌትሪክ አፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽንን 1-0 አሸንፏል።

ባለፈው ሳምንት የተካሄዱ የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታዎች ውጤት
ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 – 1 መከላከያ
አፍሮ ፅዮን 3 – 1 አዳማ ከተማ
ሠላም 1 – 1 ኢትዮጵያ ቡና
ወጣቶች አካዳሚ 1-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ሐሌታ 0 – 4 ኢትዮዽያ መድን

* ማስታወሻ

ቡድኖች ወደ ውድድር የሚገቡት በብዙ ልፋት እና ጥረት ከመሆኑ አንፃር አወዳዳሪው አካል በዳኝነት በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል ይገባል። ውድድሩ የMRI ምርመራ ተደርጎ ቡድኖች ለውድድሩ ብቁ እንደሆነ ቢገለፅም አንዳንድ ቡድኖች ከዕድሜ በላይ ተጫዋቾችን እየተጠቀሙ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። የታዳጊ ቡድኖች ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን የተጫዋች ቅያሪ እስከ አምስት የሚሆንበት አሰራር ከግምት ቢገባም መልካም ነው እንላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *