የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት አምስተኛ ቀን ውሎ

ከማሊ ጨዋታ አስቀድሞ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማድረግ ቀጠሮ የያዘው በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ቀጥሏል።

ባሳለፍነው ረቡዕ በይፋ ዝግጅቱን የጀመረው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አምስት ቀናት ባስቆጠረው የዝግጅት ቆይታው አንድ ቀን በንግድ ባንክ ሜዳ በቀሩት ቀናት ደግሞ በአዲስ አበባ ስታድየም በቀን አንድ ጊዜ ልምምዱን እየሰራ ይገኛል። በጥሩ መንፈስ ልምምዱን እየሰራ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ ከያሬድ ከበደ መጠነኛ ጉዳት በቀር ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

አምስት ቀን በቆየው የዝግጅት ጊዜ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና ረዳቶቻቸው 33ቱን ተጫዋቾች በሦስት ምድቦች በመክፈል እና በሙሉ ሜዳ በማጫወት የተጫዋቾቹን አቅም ለመለካት ጥረት እያደረጉ መሆኑን መመልከት ችለናል። ተጫዋቾቹም ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት ዕድል ለማግኘት ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ ይገኛሉ።

የመጀመርያው ምድብ ጠንካራ ስብስብ የያዘ እንደሆነ መገመት የሚያስችል ሲሆን ያካተታቸው ተጫዋቾችም ግብጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ ፤ ተከላካዮች እኔው ካሳሁን ፣ ደስታ ደሙ ወንድሜነህ ደረጄ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፤ አማካዮች ቴዎድሮስ ታፈሰ ፣ አማኑኤል ዮሐንስ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፤ አጥቂዎች በረከት ደስታ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና አቡበከር ናስር ናቸው።

በሁለተኛው ምድብ ደግሞ ግብጠባቂ ጆርጅ ደስታ ፤ ተከላካዮች ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ ዳዊት ወርቁ ፣ ሸዊት ዮሐንስ አማካዮች ሐብታሙ ተከስተ ፣ ዜናው ፈረደ ፣ ከነዓን ማርክነህ ፤ ፤ አጥቂዎች እዮብ ዓለማየሁ ፣ አሚን አህመድ እና እስራኤል እሸቱ ሲገኙ የመጨረሻው ምድብ ግብጠባቂ ምንተስኖት አሎ ፤ ተከላካዮች ይበልጣል ሽባባው ፣ ኢብራሂም ሁሴን ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ ፤ አማካዮች አፈወርቅ ሀይሉ ፣ አብስራ ተስፋዬ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፤ አጥቂዎች ሐብታሙ ገዛኸኝ ፣ ፍቃዱ ዓለሙ እና ስንታየው መንግስቱ የተካተቱበት ሆኗል።

አሰልጣኝ አብርሃም ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የሲሸልስ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለአንድ ሳምንት በሚኖረው የአዲስ አበባ ቆይታ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን የሚያደርግ ይሆናል። በወጣው መርሀግብር መሠረትም የመጀመርያው ጨዋታ መጋቢት 4 ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ መጋቢት 7 በአዲስ አበባ ስታድየም የሚካሄዱ ይሆናል። ከዚህ ጨዋታ በማስከተል 11 ተጫዋቾች የሚቀነሱ ሲሆን ቀሪዎቹ 23 ተጫዋቾች በቀጣይ ከማሊ ጋር ለሚኖረው የደርሶ መልስ ጨዋታ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አብረው የሚቆዩ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *