ባሰናበቷቸው ተጫዋቾች ምትክ ለማስፈረም በሰፊው ወደ ገበያ የወጡት ስሑል ሽረዎች ዮናስ ግርማይ፣ አርዓዶም ገብረህይወት እና ሐብታሙ ሽዋለምን አስፈርመዋል።
በዓመቱ መጀመርያ ከዓመታት የእንግሊዝ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለመቐለ 70 እንደርታ ፊርማውን ያኖረው አርዓዶም ገብረህይወት ለቀጣይ ስድስት ወራት ከስሑል ሽረ ጋር ለመቆየት ተስማምቷል። በእንግሊዙ የታችኛው ዲቪዝዮን ክለብ ፋየር ዩናይትድ ጨምሮ በትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ ባንኮች የተጫወተው አጥቂው በዚህ የዝውውር መስኮት ከቢስማርክ አፒያ እና ብሩክ ገብረዓብ ቀጥሎ ለስሑል ሽረ ፌርማው ያኖረው የማጥቃት ባህርይ ያለው ተጫዋች ሆኗል።
ሌላው ከመቐለ 70 እንደርታ ወደ ስሑል ሽረ የተቀላቀለው የተከላካይ ክፍል ተጫዋቹ ዮናስ ግርማይ ነው። ባለፈው ዓመት መጀመርያ ኢትዮጵያ መድንን ለቆ መቐለን የተቀላቀለው ይህ የቀድሞ የዳሽን ቢራ እና ትራንስ ኢትዮጵያ ተከላካይ በድጋሚ ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር የሚገናኝ ይሆናል።
በዚህ ዓመት መጀመርያ በትግራይ ዋንጫ ከአክሱም ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ጎል አስቆጥሮ ዓመቱን የጀመረው ይህ ተከላካይ በውድድር ዓመቱ በመቐለ የተሰላፊነት ዕድል አላገኘም።
ሶስተኛው ለስሑል ሽረ ፊርማውን ያኖረው የአማካይ ክፍል ተጫዋቹ ሐብታሙ ሽዋለም ነው። በትላንትናው ዕለት ከአዳማ ከተማ ጋር በስምምነት የተለያየው ቀድሞ የአውስኮድ እና ወልዲያ ተጫዋች በዚህ የዝውውር መስኮት በርካታ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች ላሰናበቱት ስሑል ሽረዎች አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡