ባሳለፍነው ማክሰኞ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ ያወጣው ፌዴሬሽኑ ለመጨረሻ አራት እጩዎች ነገ የቃልና የፁሑፍ ፈተና ለማድረግ ጥሪ አድርጎላቸዋል።
በጃፓኗ መዲና ቶኪዮ የሚከናወነው የ2020 ኦሊምፒክ በሴቶች እግርኳስ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ከዩጋንዳ ጋር በመጋቢት ከ23 እስከ መጋቢት 30 ባሉት ቀናት በደርሶ መልስ የሚያከናውን ሲሆን የመጀመርያው ጨዋታውን በአዲስ አበባ የሚያደርግ ይሆናል። ለዚህም ዝግጅት ይረዳ ዘንድ ከወዲሁ አሰልጣኝ ለመቅጠር ባለፈው ማክሰኞ የቅጥር ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ አምስት ተወዳዳሪዎች ሲቪያቸውን ያስገቡ ሲሆን እነርሱም ሰርካዲስ እውነቱ (ጥረት)፣ መሠረት ማኒ(አዲስ አበባ) ፣ ሠላም ዘርዓይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ በኃይሏ ዘለቀ (ክለብ አልባ) እና ህይወት አረፋዓይኔ (መቐለ ሰባ አንድርታ) ሆነዋል።
የቴክኒክ ኮሚቴው በቀረበው መስፈርት መሠረት አሁን ለመጨረሻ ፈተና እጩ ሆነው አራት ተወዳዳሪዎች ቀርተዋል። መሰረት ማኒ፣ ሰርካዲስ እውነቱ፣ ሠላም ዘርዓይ እና ህይወት አረፋዓይኔ የቀረቡ ሲሆን የመጨረሻ አንድ አላፊዎን ለመለየት ነገ በ08:00 ለቃል እና የጽሑፍ ፈተና በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲገኙ ጥሪ ያደረገው ቴክኒክ ኮሚቴው አሰልጣኟን በቅርቡ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ ዩጋንዳን አሸንፋ ካለፈች በቀጣዩ ዓመት መጀመርያ ከካሜሩን ጋር በሁለተኛ ዙር ማጣርያ የምትገናኝ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡