የከፍተኛ ሊጉ አንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በፎርፌ ተጠናቀቀ


በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 11ኛ ሳምንት ዛሬ እንደሚካሄድ ሲጠበቅ የነበረው የአርባምንጭ ከተማ እና ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ጨዋታ ሳይከናወን ቀርቷል።

ከእሁድ ወደ ሰኞ የተሻገረው ጨዋታ 9:00 ላይ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ቡድን ሜዳ ላይ ባለመገኘቱ ለ30 ደቂቃዎች ተጠብቆ የጨዋታ መጠናቀቅ ፊሽካ በማሰማት አርባምንጮች እና የዕለቱ ዳኞች ከሜዳው ለቀዋል። ጨዋታው መጠናቀቁን ተከትሎ በቀጣይ የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል ውሳኔ የሚጠበቅ ሲሆን የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ እና የሌሎች የምድቡ ቡድኖችን ቅሬታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ አቅርበዋል።

የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ኮሎኔል ተክሉ አወዳዳሪው አካል የጨዋታው ቀን ላይ በቅድሚያ ሊያስብበት ይገባ ነበር ሲሉ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። “በተደጋጋሚ ለከፍተኛ ሊጉ አወዳዳሪ የውድድሩን ቀን እንዲለውጥ ጠይቀን ነበር። ይህም የሆነው ከቡታጅራ ጋር የነበረው ጨዋታ በዝናብ ምክንያት በአንድ ቀን በመራዘሙ የኛ ቡድን ግጥሚያውን አከናውኖ የሚመለስበት ጊዜም በአንድ ቀን ተራዝሟል። ይህንን ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል። ለቀጣይ ጨዋታ ወጪ ለማውጣት የዚህኛው መወራረድ ይኖርበታል። አወዳዳሪው አካል ውሳኔውን አጢኖ ረቡዕ ወይም ከዛ በኋላ እንድንጫወት ማድረግ ይችል ነበር ብዬ አምናለው። ” ብለዋል።

በምድቡ የሚገኙት አንዳንድ ቡድኖችም ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት አወዳዳሪው አካል የጨዋታውን ቀን ማራዘሙ ካልቀረ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ጥያቄ መቀበል ነበረበት፤ ጨዋታው ፎርፊ ከሆነ አርባምንጭ በነጥብም ሆነ በግብ ተጠቃሚ ነው የሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *