የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና ከከፍተኛ ሊጉ የተመረጡ ተጫዋቾች …

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 34 ተጫዋቾችን በመያዝ ከማሊ ጋር ለሚያደርገው የማጣርያ ጨዋታ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ይገኛል።

በአብርሀም መብራቱ አሰልጣኝነት የሚመራው ኦሊምፒክ ቡድኑ በሀገሪቱ ሁለተኛ የሊግ እርከን ከሆነው ከፍተኛ ሊግ 8 ተጫቾችን ያካተተ ሲሆን የሚዲያ እና የመልማዮች ዝቅተኛ ትኩረት ከሚሰጠው ሊግ ለሚመረጡ ተጫዋቾች ቀጣይ የእግርኳስ ህይወት በጎ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ይገመታል።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ያለፉትን ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር እና ባለደረቦቻቸውንም ወደ ስታድየሞች በማሰማራት ለኦሊምፒክ ቡድኑ እና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ሲመለከቱ ቆይተዋል። በዚህም ከከፍተኛ ሊጉ ተጫዋቾችን አካተው ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። አሰልጣኝ አብርሀም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ሊጉ በወጣቶች የተሞላ እነረደሆነ ግምት ቢያሳድሩም ከግምታቸው የተለየ ነገር እንደተመለከቱ ተናግረዋል። ” ውድድሩ ጥሩ ነው። እርስ በርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ፉክክር ያለው እና በውጥረት የተሞላ ነው፤ የክለቦቹ ደረጃም ተቀራራቢ ነው። ግን መጀመርያ የነበረኝ ግምት በታችኛው ሊግ የሚገኙት ተጫዋቾች አብዛኛው ወጣቶች ይሆናሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፤ በእርግጥ አሁንም አሉ። በአንፃራዊነት ግን ለረጅም ጊዜ የተጫወቱ እና በእግር ኳስ የመጨረሻ ጊዜያቸው መጨረሻ የሚገኙ ብዙ ተጫዋቾች አሉ። ካየናቸው ጨዋታዎች ስምንት የሚደርሱ ተጫዋቾችን መርጠናል። ” ብለዋል አያይዘውም የተጫዋቾች ከዚህ ሊግ መመረጥ የሚያስተላልፈው መልዕክት እንዳለ ገልፀዋል። “በዚህ አጋጣሚ ለብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ በፕሪምየር ሊጉ መጫወት ግዴታ እንዳልሆነ ሁሉም በሀገሪቱ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች እንዲያውቁት እፈልጋለሁ። ይሄ መታወቅ አለበት። ኳስ መጫወት የሚችል ሰው እድሉ በተለያየ ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን እስከታችኛው ሊግ ድረስ በመውረድ ከዚህ በተጨማሪ ክልሎች የሚዘጋጁት ውድድር ላይም በመገኘት ተጫዋቾችን ለማየት እንሞክራለን። እዚህ የተመረጡ ተጫዋቾችም እዚ ልምምድ ተካፍለው አቅማቸው ከፈቀደ ይጫወታሉ፤ ባይጫወቱ እንኳ ልምዱን ወስደው ይመለሳሉ ስለዚህ ወደ ፊትም እኔ ይሁን ሙሉ የአሰልጣኞች አባላት ጨዋታዎች በስፋት እንመለከታለን። ”

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ለረጅም ዓመታት ከተጫወቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች መበራከት በጉልህ ይስተዋላል። አሰልጣኝ አብርሀምም ይህንን እንደታዘቡ እና የብቃት ደረጃቸው ዝቅተኛ እና የወጣቶችን ዕድል የሚዘጋ መሆኑን አስረድተዋል። ” ደጋግሜ እንደምለው የውጭ ተጫዋቾች ከኛ ተጫዋቾች የተሻሉ ከሆኑ ወደ ሀገራችን መምጣታቸው ምንም ክፋት የለውም። ግን ታችኛው ሊጎች ላይ የማያቸው የውጭ ተጫዋቾች አብዛኞቹ እኛ ሊግ ላይ መጫወት የማይገባቸው ናቸው። በትክክል ኳስ አቁሞ ማቀበል የማይችል ተጫዋች ለምንድነው ከውጭ የምናመጣው።
ታችኛው ሊግ ላይ ቢያንስ ለሀገራችን ወጣት ተጫዋቾች ዕድል ሰጥተው ለዋናው ሊግ ማዘጋጀት እና ማብቃት ነው የሚሻለው። ስለዚህ በዚ በኩል ያየኋቸው የውጭ ተጫዋቾች የወጣቱን በር የዘጉ ነው የሚመስለኝ። ” ሲሉ አስተያየታቸውነ አጠቃለዋል።

የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኢብራሂም አህመድ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ሊጉን በወጣቶች የተሞላ በማድረግ ለብሔራዊ ቡድኑ አማራጭ ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልፀዋል። ” የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በዛ ያሉ ቡድኖችን አሳታፊ የሚያደርግ እና በውስጡ በርካታ ወጣት ተጫዋቾች እንዲያሳትፍ ታስቦ የሚዘጋጅ ቢሆንም በአንዳንድ ቡድኖች ውስጥ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው እና እግርኳስን ለረጅም ዓመታት የተጫወቱ ተጫዋቾችን እየተመለከትን እንገኛለን። ይህ እንዳለ ሆኖ በዘንድሮ ዓመት እኔም እንዳየሁት አብዛኛዎቹ ቡድኖች ወጣት ተጫዋቾች ይዘዋል፤ እኛም ይህ እንዲሆን እንፈልጋለን። ከከፍተኛ ሊግ ሀገር ወክለው እንዲጫወቱ በመጠራታቸው በራሱ እንኳን ደስ አላችሁ ነው የምለው። አሰልጣኝ አብርሀም እና የስራ ባልደረቦቹ በተቻላቸው መጠን በየክፍለ ሀገሩ በመገኘት ጨዋታዋችን በመታደም ወጣቶቹን መስብሰብ መቻላቸው ትልቅ ነገር ነው። ወደፊት ቡድኖች ወጣቶች ላይ እንዲሰሩ ያቀድናቸው ነገር አለ። ይህ ተግባራዊ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድን ግብዓት የሚሆኑ በርካታ ተጫዋቾችን በማግኘት ረገድ የበለጠ ፍሬያማ እንሆናለን የሚል እምነት አለኝ።” ብለዋል።

ከ23 ዓመት በታች ቡድኑ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረ አንድ ሳምንት ያስቆጠረ ሲሆን ዛሬ እና በሳምንቱ መጨረሻ ከሲሸልስ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋር በሚያደርጋቸው ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ለማሊው ጨዋታ ብቁ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ይለያል ተብሏል። በመጨረሻው ስብስብ ውስጥ የመካተት ተስፋ ያላቸው የከፍተኛ ሊግ ተጫዋቾችም ለብሔራዊ ቡድን ስለመጠራታቸው እና ተያያዥነት ስላላቸው ጉዳዮች በዚህ መልኩ አስተያታቸውን ሰጥተዋል።

ጌቱ ኃይለማርያም (ሰበታ ከተማ)

እግርኳስን በአምቦ አካዳሚ በመጀመር አሁን ወደ ሰበታ አምርቼ እየተጫወትኩ እገኛለሁ። ለብሔራዊ ቡድን በመታጨቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ይህን እድል ተጠቅሜ ለሀገሬም ሆነ ለራሴ ጥሩ ነገር ማድረግ ነው የምፈልገው። የሚሰጠው ስልጠና ጥሩ ነው፤ ትንሽ ከለመድነው ውጪ ለየት ይላል። በአጠቃላይ እኔን ጨምሮ በከፍተኛ ሊግ ውስጥ የሚሳተፉ ወጣት ተጫዋቾች ጠንክረን በመስራት እንዲህ ዓይነት ዕድል ማግኘት እንችላለን እላለሁ።

ስንታየሁ መንግስቱ (አርባምንጭ ከተማ)

የእግርኳስ ህይወቴን በወላይታ ድቻ ጀምሬ በመቀጠል ወደ ሀላባ ከተማ በማምራት ተጫውቻለሁ። አሁን ላይ ለአርባምንጭ በመጫወት ላይ እገኛለሁ። የዘንድሮውን ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ለኦሊምፒክ ቡድን ተጫዋቾች ከከፍተኛ ሊግም ጭምር መመረጥ መቻላቸው ነው። ለውድድሩ ትኩረት መሰጠት መቻሉ ትልቅ ዕድል ነው።

አብዱልከሪም ወርቁ (ወልቂጤ ከተማ)

በልጅነቴ ነው በኒያላ ክለብ እግርኳስን የጀመርኩት። በመቀጠል ወደ መድን አምርቼ አሁን ላይ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ እየተጫወትኩ ነው የምገኘው። በዚህ ሁሉ ጊዜ አሰልጣኝ ደረጀ በላይን ማመስገን እፈልጋለው። ከመድን አምኖብኝ ሲያመጣኝ ህፃን ነህ ብሎ አልተወኝም። በወልቂጤ ውስጥ የሰጠኝ ሚናም ከፍተኛ ነው። ለዚህ ቡድን ጥሪ ያደረጉልኝ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱንም አመስግናለው። አሁን ገና 19 ዓመቴ ነው፤ በቀጣይ ህይወቴ በውጪ ሀገር የሚጫወት ተጫዋች በመሆን ደረጃዬን አሳድጌ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን በመወከል መጫወት እፈልጋለሁ።

ይበልጣል ሽባባው (ኢኮስኮ)

ኳስን አዊ ሳለሁ ነው የጀመሩኩት። ከዛም ፍኖተ ሰላም፣ አድዋ፣ አሁን ላይ ደግሞ ኢኮስኮ ነው የምጫወተው። ስልጠናውም ሆነ አቀባበሉ በጣም ጥሩ ነው። በአጭር ጊዜ ብዙ ነገር እንድሰራ እና እንዳውቅ አስችሎኛል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ። በቀጣይ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ለመቀላቀል ጠንክሬ እሰራለሁ።

ጆርጅ ደስታ (ኢትዮጵያ መድን)

ለብሄራዊ ቡድን በመመረጤ በጣም ደስ ብሎኛል። አንድ ተጫዋች የመጨረሻ ግቡ ብሔራዊ ቡድን መመረጥ ነው፤ ሃገርህ መወከል ትልቅ ነገር ነው እና በጣም ደስ ብሎኛል።

ኢብራሂም ሁሴን ( ኤሌክትሪክ)

ብሄራዊ ቡድን መመረጤ በጣም ደስ ብሎኛል። ያለኝን ነገር አውጥቼ እንዳሳይ እያደረገኝ ነው።
እዚ ብሔራዊ በድጋሚ ነው የተመረጥኩት፤ ከዚ በፊትም ተመርጬ ነበርና ደስ ብሎኛል። ስልጠናው በጣም ጥሩ ነው። በክለብ ከምናየው ትንሽ ልዩነት አለው። እስካሁን ጥሩ እየሰራን ነው።

ሰለሞን ወዴሳ (ኢትዮጵያ መድን)

ማንኛውም ተጫዋች ብሔራዊ ቡድን ሲመረጥ ደስ እንደሚለው እኔም ደስ ብሎኛል። እኔ ስጠራ የመጀመርያ ጊዜዬ አይደለም፤ ባለፈው ዓመት ለ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ተመርጬ ነበር። ከከፍተኛ ሊግ ስትመረጥ ልዩ ስሜት ነው የሚፈጥርብህ። ከፈጣሪ ጋር ለመጨረሻው 23 እመረጣለው ብዬ አስባለው። በእስካሁኑ ልምምድ ብዙ ለውጦች አሉ። ክለብ ላይ የማንሰራቸውን ልምምዶች እዚህ እየሰራን ነው። በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድን መመረጥ ልዩ ስሜት ይፈጥራል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *