ቁጥራዊ መረጃዎች በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር የተቆጠሩ ግቦች ዙሪያ – ክፍል አንድ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ተገባዶ ሁለተኛው ሊጀምር ቀናቶች ቀርተውታል። ይህንን አስመልክቶም በቀጣዮቹ ቀናት በአስራ አምስቱ ሳምንታት ከተመዘገቡ ውጤቶች የተወሰዱ ቁጥራዊ መረጃዎችን ልናካፍላችሁ ወደናል። የዛሬው ትኩረታችንም በጨዋታዎቹ የተቆጠሩት ጎሎች ላይ ይሆናል።

ከአጋማሾች አንፃር…

– በተደረጉት 120 ጨዋታዎች በአጠቃላይ ከተቆጠሩት 227 ጎሎች ውስጥ በተመጣጣኝ ሁኔታ 115ቱ በመጀመሪያ 112ቱ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ተቆጥረዋል።

– በመጀመሪያው አጋማሽ ደቡብ ፖሊስ 14 ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታ እና ሲዳማ ቡና ደግሞ 12 ግቦችን አስመዝግበዋል። በዚሁ አጋማሽ 14 ግቦች የተቆጠሩበት መከላከያ ቀዳሚው ሲሆን ደደቢት 13 ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ 12 ግቦች አስተናግደዋል።

– በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ግቦችን መቐለ እና ሲዳማ ደግሞ 11 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል። ከቡድኖቹ ደረጃ አንፃር በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ውጤት እንዲያስመዘግቡ እንደረዷቸው መመልከት ይቻላል። በዚህ አጋማሽ ከፍተኛ ግብ በማስተናገድ አሁንም መከላከያ በ12 ቀዳሚ ሲሆን ደደቢት ፣ ስሑል ሽረ እና ወላይታ ድቻ ደግሞ 11 ግቦች ተቆጥረውባቸዋል።

ባህር ዳር ከተማ በዙሩ ከተቆጠሩበት ስምንት ግቦች በሁለተኛው አጋማሽ ጎል ያስተናገደው መከላከያን ሲገጥም በተቆጠረበት የምንይሉ ወንድሙ ግብ ብቻ ነው። 

ከሳምንታት አንፃር…

– በጥቅሉ በመጀመሪያው ዙር በየሳምንቱ በአማካይ 15.3 ግቦች ተቆጥረዋል። 21 ግቦች የተስተናገዱበት 14ኛው ሳምንት ደግሞ ከፍተኛ የግብ መጠን የተመዘገበበት ሆኗል። መቐለ 70 እንደርታ መከላከያን 5-2 የረታበት ጨዋታም በዚሁ ሳምንት የተደረገ ነበር።

– ሦስተኛው ሳምንት ዝቅተኛ የግብ መጠን (10) የተቆጠረበት ሆኖ አልፏል። በዚህ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ያለግብ ሲጠናቀቁ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ የ1-0 ውጤት ተመዝግቦባቸው ነበር።

ከግብ ልዩነቶች አንፃር…

– ከተደረጉት 120 ጨዋታዎች 33 በመቶው (በቁጥር 40) የሚሆኑት በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 21 ጨዋታዎች ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ።

– በመሸናነፍ ከተጠናቀቁት 80 ጨዋታዎች 63 በመቶው (በቁጥር 50) ጨዋታዎች በአንድ ጎል ልዩነት ብቻ ተጠናቀዋል። ከሃምሳዎቹ ጨዋታዎች 37ቱ በ1-0 ውጤት የተጠናቀቁ ሆነዋል

– ከተቀሩት 30 ጨዋታዎች 20 የሚሆኑት በሁለት ግቦች ልዩነት ፣ 5ቱ በሦስት ጎሎች ልዩነት ፣ ሦስቱ በ4 ግቦች ልዩነት ሁለቱ ደግሞ በአምስት ግቦች ልዩነት ተጠናቀዋል።

– ሀዋሳ ከተማ ስሑል ሽረን ፣ ደቡብ ፖሊስ ጅማ አባ ጅፋርን 6-1 እንዲሁም መቐለ 70 እንደርታ መከላከያን 5-2 የረቱባቸው ጨዋታዎች በሰባት ድምር ግቦች ብዙ ጊዜ ኳስ እና መረብ የተገናኙባቸው ጨዋታዎች ነበሩ።

በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ከተደረጉ ጨዋታዎች አንፃር…

– ከ 120ዎቹ ጨዋታዎች ዘጠኙ የጋራ ሜዳ በሚጠቀሙ (ሀዋሳ፣ መቐለ እና አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ) ክለቦች መካከል ሲደረጉ አንዱ (ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና) በገለልተኛ ሜዳ የተደረገ ነበር። ከቀሪዎቹ 110 ጨዋታዎች ውስጥ 44 በመቶው (48 ጨዋታዎች) በባለሜዳ ቡድኖች አሸናፊነት ተጠናቀዋል። 21 በመቶው ( 23 ጨዋታዎች) እንግዳ ቡድኖች ድል ሲቀናቸው በቀሪዎቹ 39 ጨዋታዎች (35 በመቶው) ነጥብ ተጋርተዋል። ለወትሮው ከሜዳ ውጪ ነጥብ ይዞ መመለስ አዳጋች በሆነበት ሊግ ዘንንሮ ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎቻቸውን ካደረጉ ቡድኖች 56 በመቶዎቹ ያለሽንፈት ተመልሰዋል።

– ከ227 ጎሎች ውስጥ 126ቱ በባለሜዳ ቡድኖች ሲቆጠሩ ሀዋሳ ከተማ በ16 መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ በ13 ግቦች ቀዳሚ ሆነዋል።

– ከሜዳቸው ውጪ የተጫወቱ ቡድኖች ከመረብ ካገናኟቸው 76 ግቦች ውስጥ መከላከያ በአስር ግቦች የበላይነቱን ወስዷል።

ግቦች ከተቆጠሩባቸው ደቂቃዎች አንፃር…

– የየጨዋታዎቹን 90 ደቂቃዎች በምስል 3 ላይ እንደተመለከተው በሰባት ብንከፍላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግቦች (48) የተቆጠሩት ተጋጣሚዎች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ 15 ደቂቃዎች ሲቀሯቸው ወይንም በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ደቂቃዎች ላይ ነው። ብሔራዊ ቡድኖቻችን እና ክለቦቻችን በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ለእረፍት መቃረቢያ ደቂቃዎች ላይ በሚስተዋል የትኩረት ችግር ግብ ሲያስተናግዱ በተደጋጋሚ መስተዋሉ የሊጉ ነፀብራቅ ይሆን?

– በተመሳሳይ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች 46 ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ዘጠኙ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎች የተገኙ ነበሩ።

ይቀጥላል…


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *