የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 16ኛ ሳምንት ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ሲጀመር አዳማ ከተማ በሁለቱ አጥቂዎቹ ሐት-ትሪክ ታግዞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከፍፁም የበላይነት ጋር 7-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።
አዳማዎች የተገኙት ነፃ የጎል እድሎችን ሁሉ በመጠቀም ሎዛ አበራ እና ሴናፍ ዋቁማ ጎልተው ሲወጡ የፈረሰኞቹ እንስቶች ከጥረት ባለፈ የጎል ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል። ገና በጊዜ ጎል መቆጠር በጀመረው ጨዋታ በ8ኛው ደቂቃ ከሴናፍ ዋቁማ የተቀበለችውን ሎዛ አበራ በምትታወቅበት ጠንካራ ምቷ አስቆጥራ ባለ ሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ቻለች። ብዙም ሳይቆይ 11ኛው ደቂቃ በእንቅስቀሴ እና በሚቆጠሩ ጎሎች ትልቅ ሚና የነበራት ሰናይት ቦጋለ በጥሩ ሁኔታ የተጣለላትን ከፈረሰኞቹ ተከላካዮች ፈጥና በመውጣት የግብ ጠባቂዋን አቋቋም በማየት ሎዛ አበራ በግሩም ሁኔታ ለራሷም ለቡድኗም ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች።
ፍፁም በሚባል መልኩ የበላይነቱን የወሰዱት አዳማዎች ከሁለት ደቂቃ በኋላ በየጨዋታዎቹ ወደ ትክክለኛ ብቃቷ የተመለሰችው እና በደጋፊዎች ዘንድ አድናቆት ሲቸራት የዋለችው ሰናይት ቦጋለ የፈጠረችውን የጎል አጋጣሚ ግብጠባቂዋ ስትተፋው ሴናፍ ዋቁማ ኳሱን ወደ ጎልነት ቀይራው የአዳማን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርገዋለች።
ባለ ሜዳዎቹ አዳማዎች በተለይ ከሰናይት ጥሩ እንቅስቃሴ እና ከአጥቂዎቹ የመጨረስ ብቃት በተጨማሪ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት እንቅስቃሴ ለመሳተፍ በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ የግብ ዕድሎች ለመፈጠር ትልቁን አስተዋፆኦ ይወጡ እንደነበረ መመልከት ችለናል። ጊዮርጊሶች በአንፃሩ በስብስባቸው ያካተቷቸው አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ለሊጉ አዲስ እንደመሆናቸው መጠን እና በታዳጊዎች የተሞላ ስብስብ በመሆኑ ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋች መሆናቸውን ከመግለፅ ውጭ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱም በኩል ደካማ ሆነው ታይተዋል።
21ኛው ደቂቃ አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት ከራሳቸው የግብ ክልል ጀምሮ በፍጥነት አምልጣ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂዋን ጭምር በማለፍ ሎዛ አበራ ለቡድኑ አራተኛ ለራሷ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል አስቆጥራለች። ምንም የተለየ ነገር ሳይታይ በአዳማ እንስቶች የበላይነት ጨዋታው ቀጥሎ በ36ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሴናፍ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ አምስተኛ ጎል በማስቆጠር የግብ መጠናቸውን ከፍ ማድረግ ችላለች።
ከእረፍት መልስ ገና በ49ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ከግራ መስመር ያሻገረችላትን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ስድስተኛ ጎል አስቆጥራ ሐት-ትሪክ መስራት ችላለች። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተጠቀሽ የሚሆን የጨዋታው ብቸኛ የግብ ዕድል 65ኛው ደቂቃ መልካም ተፈሪ ከሳጥን ውጭ የመታችውን ኳስ ለጥቂት በግቡ ጠርዝ የወጣው ተጠቃሽ ነበር። ቀዝቀዝ እያለ በቀጠለው ጨዋታ 77ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ለራሷ አራተኛ ለቡድኗ ሰባተኛ የማሳረጊያ ጎል አስቆጥራ ከድሬደዋ አይዳ ዑስማን በመብለጥ በ14 ጎል የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምራለች።
በመጨረሻም ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል እድሎችን አዳማዎች በሎዛ እና በሴናፍ በኩል ቢያገኙም ጎል ለማስቆጠር ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት እና ጉጉት የተነሳ የማይታመኑ ነፃ የጎል እድሎችን ያመከኑ ሲሆን አዳማዎች ጨዋታውን 7 – 0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት አጠናቀዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡