ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | ንግድ ባንክ ወደ መሪነት ሲመለስ ጥሩነሽ እና ሀዋሳም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 16ኛ ሳምንት ዛሬም ሲቀጥል በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ንግድ ባንክ ወደ መሪነቱ ተመልሷል። መከላከያ ነጥብ ሲጥል ሀዋሳ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ አሸንፈዋል።
የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎች
(ዳንኤል መስፍን)

በ9:00 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንኮች 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ንግድ ባንኮች ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን 41ኛው ደቂቃ ከገነሜ ወርቁ የተሻገረውን ረሂማ ዘርጋው በግንባሯ በመግጨት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥራለች።

ከእረፍት መልስ ተቀይራ የገባችው ታሪኳ ደባስ ያቀበለቻትን ሽታዬ ሲሳይ በ49ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ስታስቆጥር በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ህይወት ዴንጊሶ 61ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሯ ገጭታ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች። ብዙም ሳይቆይ 67ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው ለቡድኗ አራተኛ ለራሷ ሁለተኛ ጎል ስታስቆጥር በጨዋታው መጠናቀቂያ ደግሞ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ረሂማ ዘርጋው ወደ ጎልነት በመቀየር በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ለቡድኗ የማሳረጊያ አምስተኛ ጎል በውድድር ዓመቱ አስራ አንደኛ ጎሏን በማስቆጠር ጨዋታው በንግድ ባንክ 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

11:00 በቀጠለው መከላከያ ከአዲስ አበባ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ብዙም ሳቢ ሳይሆን በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃዎች ድራማዊ ትዕይት አስመልክቶናል። መዲና ዐወል 89ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂዋን መውጣት ተመልክታ ቺፕ በማድረግ ግሩም ጎል አስቆጥራ መከላከያዎች ደስታቸውን ገልፀው ሳያጠናቅቁ በተጨማሪ ደቂቃ አዲስ አበባዎችን ህይወት ረጉ አቻ በማድረግ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

የክልል ሜዳዎች ውሎ
(ቴዎድሮስ ታከለ)

ሀዋሳ ላይ በሜዳው ኢትዮ ኤሌክትሪክን የጋበዘው ሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽን ቀናት በፊት ካሰናበተ በኃላ የቀድሞው አሰልጣኙ ቴዎድሮስ ደስታን የመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለአሰልጣኙ የመጀመሪያ በሆነው ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ የሀዋሳ ከተማ የጨዋታ እና የግብ ማግባት ዕድሎች ጎልተው በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል፡፡ በተለይ በመስመር እና ከተረጋጋው የአማካይ ክፍሉ በሚነሱ  ኳሶች ወደ ፊት ለአጥቂዎቹ ምርቃት ፈለቀ እና ነፃነት መና በመጣል እና በርካታ ዕድሎች በመፍጠሩ ረገድ አዋጭ አጨዋወትን መከተል ቢችሉም ያገኟቿቸውን አጋጣሚዎች ደግሞ ወደ ግብነት ለመለወጥ እጅጉን ተዳክመውም ነበር። ገና 2ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል ፈታኝ የሆነ እንቅስቃሴን በማድረግ የኤሌክትሪክን የተከላካይ ክፍል ስትረብሽ የታየችሁ መሳይ ተመስገን ፍጥነቷን ተጠቅሟ ወደ ግብ ክልል በመግባት የመታችውን ኳስ እስራኤል ከተማ ያደነችባት ቀዳሚው መከራ ነበር፡፡

መከላከል ላይ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ሲያሳልፉ የታዩት ኤሌክትሪኮች ከቆመ ኳስ ከሚገኙ አጋጣሚዎች ብቻ መሳይ ተመስገን በቀጥተኛ ኳስ ወደ ግብ ከምትልካቸው ዕድሎች ውጪ በጨዋታ ሂደት ለመፍጠር የሞከሩት አንዳች ሁኔታ ግን አልነበረም፡፡ ቶሎ ቶሎ በምርቃት፣ ወርቅነሽ እና ነፃነት መና ከተሻጋሪ ኳሶች  በተመሳሳይ በቀኝ በኩል ከዓይናለም አደራ የተላለፈላቸውን ኳሶች በቀላሉ ሲያመክኑ ተስተውሏል፡፡ 17ኛው ደቂቃ በአማካይ ክፍሉ ከመቅደስ ማሞ ጋር ጥሩ ጥምረት የነበራት ሳራ ኬዲ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈችውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረችው ምርቃት ፈለቀ ከግብ ጠባቂዋ እስራኤል ጋር ተገናኝታ እስራኤል አስጥላታለች፡፡ 27ኛ ደቂቃ ኤሌክትሪክ መልካም የሚባል ዕድልን አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ከቅጣት ምት መሳይ ተመስገን በረጅሙ ወደ ግብ ልካ በሀዋሳ ተከላካዮች ስትመለስ ወርቅነሽ ሜልሜላ ብታገኘውም ያመከነችሁ በተጨማሪነትም ከማህዘን ምት ራሷ ወርቅነሽ አሻምታ አለምነሽ ገረመው በትዕግስት አበራ የተያዘባት ክስተት ተጠቃሾች ናቸው።

30ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ፀጋ ወደ ግብ የላከችውን ኳስ ምርቃት ፈለቀ ብታስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ መባሉ ሀዋሳዎችን ባለማስደሰቱ በአምበሏ መቅደስ ማም አማካኝነት ረዳት ዳኛዋ ላይ ክስ አስመዝግበዋል፡፡ ይህ ክስተት ከተከሰተ በኃላ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ የሀዋሳዋ ተጫዋች መሳይ ተመስገን ላይ የተገቢነት ክስ አለኝ በማለት ከዳኞች ጋር ሲፈጥር በነበረው ሰጣ ገባ ከበርካታ ተመልካቾች ተቃውሞን ያስተናገደ ሌላኛው አጋጣሚ ነበር፡፡ 36ኛው ደቂቃ አረጋሽ ፀጋ በተመሳሳይ ልክ እንደተሻረችው ኳስ በቀኝ በኩል ያሻገረችውን ኳስ ምርቃት ፈለቀ የኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ እስራኤል ስህተት ታክሎበት በግንባር በመግጨት አስቆጥራ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችላ ለእረፍት ወጥተዋል፡፡

በአመዛኙ በመሐል ሜዳ ላይ የተገደበ አጨዋወትን በተመለከትንበት ሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑም ቢሆን ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም የሀዋሳ ከተማ ብልጫ አሁን ቀጥሏል፡፡ አሁንም ከቆመ ኳስ ኤሌክትሪኮች በመሳይ ተመስን ጠንካራ ሙከራዎች ዉጪ ተጨማሪ ዕድድል ለመፍጠር ግን አልቻሉም፡፡ 60ኛ ደቂቃ መሳይ ተመስገን ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ይዛ በመግባት ለነፃነት ሰታት ነፃነት ወደ ግቡ በቀጥታ የመታችሁን ኳስ ተከላካይዋ ማህደር ጋሻው ከግቡ መስመር እንደምንም ልታወጣው ችላለች፡፡ 76ኛው ደቂቃ ምርቃት አግኝታ የመታረችሁን ኳስ የግቡ ቋሚ ብረት ሊመልስባት ችሏል፡፡ ሀዋሳዎች ተጨማሪ የማግባት ሂደቶችን እንደነበራቸው ብልጫ በነፃነት ምርቃት እና መሳይ አማካኝነት ቢያገኝም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡

አሰላ ላይ ጠንካራው ጌዲኦ ዲላን ያስተናገደው ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ወሳኝ ሶስት ነጥብን ማግኘት ትሏል፡፡ ጥሩነሽ አካዳሚ 3-2 በረታበት ጨዋታ ትንሳኤ ሻንቆ እና ቅድስት በላቸው የግቦቹ ባለቤት ሲሆኑ ጌዲኦን ከሽንፈት ያላዳነችዋን ግብ ደግሞ ድንቅነሽ በቀለ ማስቆጠር ችላለች፡፡



© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *