ከነገ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነውን የአባ ጅፋር እና አዳማ ጨዋታን የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።
በመካከላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ያለው ጅማ አባ ጅፋር እና አዳማ ከተማ ነገ 9፡00 ላይ በጅማ ስታድየም ይገናኛሉ። በሰንጠረዡ አጋማሽ የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቁት ቻምፒዮኖቹ ደረጃቸውን ማሻሻል ይችሉባቸው የነበሩባቸውን የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ወደራቁበት የዋንጫ ፉክክር ለመመለስም የቀድሞው አጥቂያቸው ኦኪኪ አፎላቢን መልሰው ሲያመጡ ትናንት ደግሞ የመስመር አጥቂው ፈሪድ የሱፍን ማስፈረም ችለዋል። ከዚህ ባለፈ ክለቡ ከኤልያስ ማሞ እና ቢስማርክ አፒያ ጋር ሲለያይ ኤርሚያስ ኃይሉን ደግሞ በውሰት ለድሬዳዋ ሰጥቷል። በመስመር አጥቂዎቻቸው እንቅስቃሴ ላይ በተመሰረት የማጥቃት አጨዋወት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ባለሜዳዎቹ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች ባይኖርም ኦኪኪ የወረቀት ጉዳዮችን ባለማጠናቀቁ ዘሪሁን ታደለ ደግሞ ከጉዳት መልስ ልምምድ ባለማሟላቱ እንደማይሰለፉ ታውቋል።
በንፅፅር ሲታይ ጠንካራ እና በወጣቶች የተገነባ ስብስብ የያዘው አዳማ ከተማ ከሊጉ መሪ በ13 ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል። አዳማዎች አራት ተከታታይ ጨዋታዎቻቸውን በአቻ ውጤት በማጠናቀቃቸው በነገው ጨዋታ ውጤት ይዞ መመለስን ያለመ ወደ ማጥቃቱ ያደላ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ሆኖም የቡድኑ ከግብ ማስቆጠር መራቅ እንዲሁም በተደጋጋሚ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ከሚገቡ ተጫዋቾቹ መካከል አምስቱን ነገ ያለመጠቀሙ ጉዳይ በጨዋታው ዋነኛው ፈተናው መሆኑ አይቀርም። አዳማ ባለፉት ሳምንታት ከሀብታሙ ሸዋለም ፣ አዲስዓለም ደሳለኝ ፣ ሱራፌል ጌታቸው እና ኄኖክ ካሳሁን ጋር የተለያየ ሲሆን ብሩክ ቃልቦሬ እና አመርላ ደልታታን አስፈርሞ ብሩክ ቦጋለ እና ዳግም ታረቀኝን ደግሞ ከታችኛው ቡድኑ አሳድጓል።
አዳማ ከተማ በነገው ጨዋታ በጉዳት ቡልቻ ሹራ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና አንዳርጋቸው ይላቅን ሲያጣ ከነዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ውስጥ በመካተታቸው ሱለይማን ሰሚድ በሁለተኛ ኒጫ ካርድ ቅጣት ፣ ሮበርት ኦዶንካራ ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በመመረጡ ምክንያት የማይሰለፉ ይሆናል፡፡ በተያያዘ ዜና ያለፉትን ሦስት ቀናት በህመም ምክንያት ከክለቡ ጋር ያልነበሩት አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም ዛሬ ማለዳ ህክምናቸውን አጠናቀው ወደ ጅማ በማምራት ክለቡን ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን የሚመሩት ይሆናል።
የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች
– በ2010 ወደ ሊጉ ያደገው አባ ጅፋር እና አዳማ የተገናኙበት የመጀመሪያ ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቀ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ግን ቻምፒዮኖቹ 5-0 እና 2-0 መርታት ችለዋል።
– በሜዳቸው ሽንፈት ያላስተናገዱት ጅማዎች ሦስቴ ድል ሲያደርጉ አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ከድሬዳዋው የ3-3 ጨዋታ በኋላም ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች ጅማ ላይ ግብ አላስተናገደም።
– አዳማ ከተማ ሰባት ጊዜ ከሜዳው የወጣ ሲሆን አራቴ ነጥብ ሲጋራ አንድ የድል እና ሁለት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሽንፈት አላገኘውም።
ዳኛ
– እስካሀን በሊጉ በዳኘባቸው ሦስት ጨዋታዎች ስምንት የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶች የመዘዘው እያሱ ፈንቴ ይህን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ዳንኤል አጄዬ
ዐወት ገ/ሚካኤል – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ
ኄኖክ ገምቴሳ – ይሁን እንዳሻው – መስዑድ መሀመድ
ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ጃኮ ፔንዜ
ሱራፌል ዳንኤል – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ
ዐመለ ሚልኪያስ – ኢስማኤል ሳንጋሪ
ኤፍሬም ዘካርያስ – አዲስ ህንፃ – ፋዓድ ፈረጃ
ዳዋ ሆቴሳ