የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 0-2 ደቡብ ፖሊስ

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው ብቸኛ የሊጉ ጨዋታ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መዲናዋ የመጣው ደቡብ ፖሊስ መከላከያን በመርታት ዳግም ሦስት ነጥቦችን ሸክፎ ተመልሷል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተሰጡ አስተያየቶችን እንሆ …

” ውጤቱ ለኛ የከፋ ነው ” ሥዩም ከበደ – መከላከያ

ስለጨዋታው

ለኛ ጥሩ ቀን አልነበረም። ሁለተኛው ዙር እያንዳንዱ ጨዋታ ወሳኝ ነው። እኛ ጋር የምናስተናግዳቸው ግቦች ቡድኑን ይዞ የመውረድ ነገር አላቸው። ትልቁ ክፍተታችንም እሱ ነበር። ከዛ ለመውጣትም ጥረት አድርገናል። ደቡብ ፖሊሶች የገኟቸው ግቦች ለነሱ በቂ ስለነበሩ ሁለተኛው አጋማሽ ላይጥንቃቄን መርጠው ነበር ፤ እኛም ለማጥቃት ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር። ውጤቱ ለኛ የከፋ ነው። በጉዳት እና በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ያጣናቸው ተጫዋቾች ሲመለሱ የተሻለ ነገር እንደሚኖር አስባለው።

በቡድኑ የመከላከል ችግር ላይ የነበረው የአማካይ ክፍሉ ድክመት

የአማካይ ክፍላችን ቅርፅ እንደጠበቅነው አልነበረም። ለምሳሌ እነሱ 4-3-3 ሲጫወቱ እኛ መሀል ላይ አራት ተጫዋቾች ነበሩን። ግን ሦስቱን የመሀል ተሰላፊዎች ለመቆጣጠር ያሳደርነው ጫና ልክ አልነበረም። ጨዋታዎችን ለማስቀረፅ እየሞከርን ነው። ከዛ ተነስተን በማስተማር ተጫዋቾችንም እየቀየር በመሞከር ለማስተካከል የምንሞክር ይሆናል።

” ባሰብነው መንገድ ተጫውተን ውጤቱን አግኝተናል” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ደቡብ ፖሊስ

ስለጨዋታው እና ስለቡድኑ

ካለንበት ደረጃ መውጣት የምንችለው ይህን ጨዋታ ስናሸንፍ መሆኑን እናውቅ ነበር ፤ በዚህ ምክንያት ተዘጋጅተን ነው የመጣነው። ባሰብነው መንገድ ተጫውተንም ውጤቱን አግኝተናል። ቡድኑ ጥሩ ተጫዋቾችን የያዘ ነው ፤ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው። የጎደላቸው ተነሳሽነት ብቻ ነበር። ተነሳሽነታቸውን ከፍ በማድረግም ውጤት እንደምናመጣ አስባለው።

የተፈጠሩ መልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን በአግባቡ አለመጠቀማቸው ከጨዋታ ዕቅዳቸው አንፃር

መልሶ ማጥቃት የዕቅዳችን አካል አልነበረም። ሆኖም የጨዋታ ዕቅዶችን በመሀል የሚፈጠሩ ሁኔታዎች ሊመሯቸው ይችላሉ። በዛ ምክንያትም መቆራረጦች ይታያሉ። ተጫዋቾቹ በኔ አጨዋወት ይህ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ነው። እስኪላመዱም ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ከዛ የተነሳ የተከሰተ እንጂ ሌላ አልነበረም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *