ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | ንግድ ባንክ በሜዳው፤ አዳማ እና ሀዋሳ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 17ኛ ሳምንት ዛሬ አራት ጨዋታዎች ሲከናወኑ መሪው ንግድ ባንክ እና ተከታዩ አዳማ ከተማ ድል ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ ሲያሸንፍ ድሬዳዋ እና ጥሩነሽ አካዳሚ ነጥብ ተጋርተዋል።

በአዲስ አበባ ስታድየም 09:00 ላይ በንግድ ባንክና በመከላከያ መካከል የተካሄደው ጨዋታ በንግድ ባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ መልካም የሚባል የውድድር ዘመን እያሳለፈች የምትገኘው የመከላከያዋ አማካይ እመቤት አዲሱ በሴቶች ስፖርት ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ በሚሰራው ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት ሚድያ የወሩ ኮከብ ሽልማት ተበርክቶላታል።

ጠንካራ ፉክክር በተስተናገደበት በዚህ ጨዋታ ኳሱን ይዞ በመጫወት መከላከያዎች የተሻሉ ቢሆኑም የጎል አጋጣሚ በመፍጠር በኩል ንግድ ባነኮች ቀዳሚ ነበሩ። 6ኛው ደቂቃ ህይወት ደንጊሶ ከሳጥን ውጭ የመታቸው ጠንካራ ኳስ የግቡ አግዳሚ ሲመልሰው ብዙነሽ ሲሳይ ብቻዋን ነፃ የግብ ዕድል አግኝታ ባለመረጋጋቷ የተነሰ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

የጨዋታው እንቅስቃሴ አንዴ ፈጠን አንዴ ቀዝቀዝ እያለ ወደ ጥንቃቄ ቢያመራም በመልሶ ማጥቃት ረሂማ ዘርጋው በመከላከያ የሜዳ ክፍል ያገኘችውን ኳስ በረኛዋን ማርታ በቀለን በማለፍ ወደ ጎል ብትመታውም ኳስ በማጠሩ ፋሲካ እንደምንም ደርሳ አውጥታዋለች።

በአማካዮቹ እመቤትአዲሱ፣ ሲሳይ ገ/ዋህድ እና የካቲት ጥሩ ጥምረት የሄደውን ኳስ ሔለን እሸቱ ተቀብላ ያሻገረችውን በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመግባት ጎሎችን ወደማስቆጠር የመጣችው መዲና ዐወል 22ኛው ደቂቃ ላይ ግብጠባቂዋ ንግስቲን በማለፍ ግሩም ጎል ለመከላከያ አስቆጥራለች።

በጨዋታው አጋጣሚ የመስመር ዳኛዋ ጽድቅነሽ አበራ ባጋጠማት ድንገተኛ ጉዳት በአራተኛዋ ዳኛ ለመተካት ተገዳ በቀጠለው ጨዋታ ንግድ ባንኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው ለመጫወት በሚያደርጉት ጥረት ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ህይወት ደንጊሶ አቻ ማድረግ የምትችልበትን ኳስ በግንባሯ ብትመታውም ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ ይዛባታለች። ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ መከላከያ የነበረውን የኳስ ቁጥጥር ማስጠበቅ አቅቷቸው ወደ ኃላ በማፈግፈጋቸው 43ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ሽታዬ ሲሳይ በቀጥታ ወደ ጎልነት በመቀየር ንግድ ባንክን አቻ ማድረግ ችላለች።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ጠንካራ ፉክክር ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል እንደምንመለከት ቢጠበቅም ከቆሙ ኳሶች ከሚፈጠሩ የግብ ዕድሎች ውጪ የረባ እንቅስቃሴ መመልከት ሳንችል ቀርተናል። 67ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ወደ መከላከያ የግብ ክልል የተጣለውን ኳስ ረሂማ ዘርጋው የግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለን ስህተት ተጠቅማ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራ ንግድ ባንክን መሪ ማድረግ ችላለች።

መከላከያ በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ሆኖ እንዲታይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበሩት ሲሳይ እና አረጋሽን አሰልጣኝ በለጠ ገብረ ኪዳን መቀየራቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ንግድ ባንኮች ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጠንካራ መከላከል እና የግብ ጠባቂዋ ንግስቲ ንቃት ታክሎበት ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት አስችሏቸዋል።

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopia

11:00 በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ እንግዶቹ ሀዋሳዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን 4 – 0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል።

መሳይ ተመስገን በግል ጥረቷ የምትፈጥረው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ለሀዋሳ እንስቶች ጥንካሬ፤ ለፈረሰኞቹ ተከላካዮች ፈታኝ ነበር። መሳይ በቀኝ መስመር በፍጥነት ገብታ ነፃ አቋቋም ለምትገኘው ምርቃት ፈለቀ ብታቀብላትም ግብ ጠባቂዋን በማለፍ ጎል ለማስቆጠር ስታስብ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

10ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ምርቃት ፈለቀ በአግባቡ ተጠቅማ ወደ ጎልነት በመቀየር ሀዋሳዎችን መሪ ማድረግ ችላለች። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ኳሱን በጥሩ ሁኔታ ይጫወቱት እንጂ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ታዳጊዎች በመሆናቸው ኳሱን የማራቅም ሆነ በጉልበት ከሀዋሳ ጋር መመጣጠን ባለመቻላቸው ኳሱን በቀላሉ እየተነጠቁ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ለመመልከት ችለናል።

በሀዋሳዎች በኩል ምንም የተለየ ነገር ሳንመለከት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቆ ከእረፍት መልስ 60ኛው ደቂቃ ከምርቃት ፈለቀ በጥሩ መንገድ የተሰጣትን ነፃነት መና ሁለተኛ ጎል ስታስቆጥር በመቀጠል በ65ኛው ደቂቃ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ምርቃት ፈለቀ ወደ ጎልነት በመቀየር የሀዋሳዎችን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጋዋለች። 78ኛው ደቂቃ ሌላ አራተኛ ጎል ነፃነት መና አስቆጥራለች። በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው አንድ የጎል ሙከራ መፍጠር ሳይችሉ በእንግዶቹ ሀዋሳዎች 4-0 ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።

በክልል ስታድየሞች በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ወደ ዲላ አምርቶ ጌዴኦ ዲላን 2-1 ማሸነፍ ችሏል። አዲስ ፈራሚዋ ሎዛ አበራ ሁለቱንም ጎሎች በማስቆጠር ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት የሚፎካከሩ ተጫዋቾችን መቅረብ ችላለች።

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ዕድላዊት ተመስገን እና ስራ ይርዳው ለድሬዳዋ፣ ኝቦኝ የን እና ትንሳኤ ሻንቆ ለጥሩነሽ የጎሎቹ ባለቤቶች ናቸው።

የሊጉ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ አርባምንጭ ላይ በ9:00 አርባምንጭ ከተማ ከ ጥረት ኮርፖሬት፣ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ11:00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አዲስ አበባ ከተማ ይጫወታሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply